በታችኛው ኦሞ ሸለቆ የሚካሄዱ የልማት ስራዎች የዓለም አቀፍ ቅርሶችን ደህንነት በጠበቀ መልኩ ሊሆን ይገባል

187

ጂንካ፤የካቲት 8/2014(ኢዜአ) በታችኛው ኦሞ ሸለቆ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች በአካባቢው የሚገኙ ዓለም አቀፍ ቅርሶችን ደህንነት በጠበቀ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ ተመላከተ።

የታችኛው ኦሞ ሸለቆ ቅርሶችን ዘላቂ ደህንነት ለማረጋገጥ በተዘጋጀ ረቂቅ የአስተዳደር ዕቅድ ሰነድ ላይ የፌዴራል ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ከጂንካ ዩኒቨርሲቲ እና ባለድርሻ አካላት ጋር በጂንካ ከተማ  ውይይት እያካሄደ ነው።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም  ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አቡቶ አሊቶ፤ታሪካዊ ቅርሶችና ጥንታዊ የሰው ዘር መገኛ የሆነውን የታችኛው ኦሞ ሸለቆ በመንከባከብ መጠበቅ ይገባል ብለዋል።

በደቡብ ክልል በአለም ቅርስነት ከተመዘገቡት ሦስት ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች አንዱ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ ነው ያሉት አቶ አቡቶ፤ ቅርሱ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበ ቢሆንም እንደ አለም ቅርስነቱ ተገቢውን ጥበቃ እየተደረገለት አለመሆኑን ተናግረዋል ።

ቅርሱ በሚገኝበት አካባቢ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ደህንነቱ ላይ ተፅዕኖ እያደረጉበት መሆኑን ጠቁመው የልማት ስራዎቹ  የቅርሱን ደህንነት በጠበቀ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል።

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኩሴ ጉድሼ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው በታችኛው የኦሞ ሸለቆ የሚገኙ ቅርሶች ደህንነት የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነት አለበት ብለዋል።

በቅርሶቹ ደህንነት ዙሪያ ከባለስልጣኑ ጋር በመሆን ጥናታዊ ስራዎችን በማካሄድ ቅርሱን ለመጠበቅና ለመንከባከብ የሚረዳ የአስተዳደር ረቂቅ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

ለሶስት ቀናት በሚቆየው መድረክ በተዘጋጀው ረቂቅ የአስተዳደር ሰነድ ላይ ውይይት የሚካሄድ ሲሆን፤  በዚህም ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ያሉ የሚመለከታቸው አካላት እንዲሁም በቅርሶቹ አከባቢ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮች እየተሳተፉ ነው።