በተፈጥሮ ሃብት ህልውና ላይ አደጋ የደቀኑ መጤ አረሞችን ለማጥፋት ሁሉን አቀፍ ንቅናቄ ያስፈልጋል

72

የካቲት 8/2014/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብት ህልውና ላይ አደጋ የደቀኑ መጤ አረሞችን ለማጥፋት ሁሉን አቀፍ ንቅናቄ ማድረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

በዝዋይ ሃይቅ ላይ ተስፋፍቶ የሚገኘውን የእምቦጭ አረም ለማጥፋትና በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ላይ የደቀነውን አደጋ ለመከላከል የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በባቱ ከተማ ተካሂዷል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታሁን ጋረደው በዚህ ወቅት እንዳሉት በአገሪቱ የውሃ ሀብት ላይ እየተስፋፋ ያለውን የእምቦጭ አረም ለማጥፋት የሁሉም ህብረተሰብ ትብብር ይጠይቃል።

መጤና ወራሪ አረሞችን በአንድ ተቋም ብቻ ማስወገድ ስለማይቻል ሁሉም ባለድርሻ አካላትና የህዝቡ ትብብር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለዚህም ህብረተሰቡ፣ የተለያዩ ተቋማት፣ አደረጃጀቶች በጋራ መስራት ያስፈልጋል ሲሉም ገልጸዋል።

በአካባቢ ጥበቃ፣ አካባቢን ከብክለት ለመጠበቅና መጤ ወራሪ አረሞችን ለመከለካል የአስር ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ መዘጋጀቱንና ይህንንም ለመከወን የህዝብ ንቅናቄ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዝዋይ ሀይቅ ላይ እምቦጭ በመንቀል የተሳተፈው የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ፕሬዝዳንት አስፋው ተክሌ፤ ወጣቶች በአገሪቱ ልማት ውስጥ እያደረጉ ያለው አስተዋፆ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብሏል።

አሸባሪው ህወሓት ለመደምሰስ በተደረገው ጥረት ላይ ወጣቶች ትልቅ ድርሻ እንደነበራቸው ጠቅሶ በልማት ስራዎችም ተሳትፏቸን መጠናከር አለበት ብሏል።

በአካባቢ ጥበቃ ላይ ባለቤት ሆኖ ወጣቶች በትኩረት መስራት አለባቸው ያለው ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ የጽህፈት ቤት ሃላፊ አክሊሉ ታደሰ ነው።

ወጣቶች በአገሪቱ በሚከናወኑ የልማት ስራዎች ላይ በስፋት መሳተፍ ይጠበቅባቸዋልም ብሏል።

እምቦጭን ከዝዋይ ሀይቅ ላይ በመንቀል የተሳተፉት ወጣቶቹ እንደ ሌሎች የልማት ስራዎች በአካባቢ ጥበቃ ላይ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም