ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ “ለዓመቱ ምርጥ የአፍሪካ ወጣት” ሽልማት በእጩነት ቀረቡ

109

የካቲት 8 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ “በፊውቸር አፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ወጣት” ሽልማት ውስጥ በእጩነት ቀረቡ።አፍሪካውያን ወጣቶችን በማስተሳሰር የአህጉሪቷን ችግሮች ለመቅረፍ የሚንቀሳቀሰው “ዘ ፊውቸር አፍሪካ” ፕሮጀክት የ16ተኛው ዘ ፊውቸር ሽልማት እጩዎችን ይፋ አድርጓል።

ታዋቂው የእግር ኳስ ተጫዋች ሞሐመድ ሳላህን ጨምሮ አምስት አፍሪካውያን በተካተቱበት የእጩዎች ዝርዝር ውስጥ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜም ተካተዋል።

ለሽልማቱ በእጩነት መመረጣቸውን ተከትሎ ኮሚሽነሯ ባስተላለፉት መልዕክት “በሽልማቱ እጩ ዝርዝር ውስጥ በመካተቴ ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል፣ ለፕሮጀክቱም ምስጋናዬን አቀርባለሁ” ብለዋል።

በእጩነት ከቀረቡት ውስጥ የዚምቧቡዌና የናይጄሪያ ስራ ፈጣሪዎችና ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ወጣቶች ይገኙበታል።

መቀመጫውን በሌጎስ ናይጄሪያ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው “ዘ ፊውቸር አፍሪካ” አፍሪካውያን ወጣቶችን በማስተሳሰር በአፍሪካ አንገብጋቢ የሆኑትን የመልካም አስተዳደርና የስራ አጥነት ችግርን ለመፍታት እንደሚንቀሳቀስ መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም