ዳያስፖራዎች ለሰሜን ወሎ ዞን ተፋናቃዮች 18 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ድጋፍ አደረጉ

75

የካቲት 7 ቀን 2014(ኢዜአ) ዳያስፖራዎች በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ለሚገኙ ተፋናቃዮች የ18 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብና ሌሎች ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረጉ።


በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ለመደገፍ በአይዞን ኢትዮጵያ ዶት ኮም መተግበሪያ ገንዘብ እያሰባሰቡ ይገኛል።     

በዚሁ የገንዘብ ማስተላለፊያ በኩል እስካሁን 7 ሚሊዮን ዶላር ሲሰበሰብ ከዚሁ ገንዘብ ላይ በአማራ ክልል ቆቦ ወረዳ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደርጓል።

ከአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽንና ዳያስፖራ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ድጋፉ ለተፈናቃይ ወገኖች አንዲደርስ የተደረገ ሲሆን የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደበበ ዘውዴ፤ ድጋፉ የመጀመሪያው ዙር መሆኑን አብራርተዋል።

በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን በመደገፍ ረገድ ጠንካራ አቅም መሆናቸውንም ጠቅሰው በቀጣይነት ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።    

"ከጦርነቱ በኋላ ያለው መልሶ ግንባታና ማቋቋም ትልቅ በጀት ይጠይቃል ያሉት አቶ ደበበ ዳያስፖራው በመሰረተ ልማት፣ የትምህርትና የጤና ተቋማት መልሶ ግንባታ ላይ ጠንካራ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።    

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ምክትል ሃላፊ እታገኘሁ አደመ፤ በዳያስፖራዎች ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው ዜጎች መልሰው እንዲቋቋሙና ከወቅታዊ ችግሮች እንዲሻገሩ የሁሉም ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

የድጋፉ አስተባባሪና በዋሽንግተን ዲሲ የሰላምና አንድነት የኢትዮጵያ ግብረ ሃይል አባል አቶ ዮሃንስ ጉርሙ፤ ኢትዮጵያዊያን ያደረጉት ድጋፍ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ሕይወት እየታደገ መሆኑን ተናግረዋል።      

አሸባሪው ህወሃት በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች በተለይም ሴቶች፣ ህጻናትና እናቶች ላይ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት በመፈፀም የከፋ ችግር ላይ እንዲወድቁ ስላደረጋቸው ወደ ቀደመ ኑሯቸው እስከሚመለሱ ድረስ ሁላችንም በምንችለው አቅም መደገፋችንን መቀጠል አለበን ብለዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም