በአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ የተላለፈው 'ኤች አር 6600' የውሳኔ ኃሳብ ወገንተኝነት የታየበት ነው

73

የካቲት 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ በቅርቡ ያሳለፈው 'ኤች አር 6600' የተሰኘው የውሳኔ ኃሳብ ትክክል ያልሆነና ወገንተኝነት የተንጸባረቀበት ነው ሲል የኢትዮጵያ አሜሪካውያን ዜጎች ምክር ቤት ገለጸ።

ባሳለፍነው ሣምንት የአሜሪካው ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ በኢትዮጵያ የሰላምና የዴሞክራሲ ግንባታ ለመደገፍ በሚል 'ኤች አር 6600' የተሰኘ የውሳኔ ኃሳብ አሳልፏል።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ አሜሪካውያን ዜጎች ምክር ቤት ሊቀመንበር ዲያቆን ዮሴፍ ተፈሪ የውሳኔ ኃሳቡ ሕወሃትን ለማትረፍ የሚፈልጉ ወገኖች ያዘጋጁት ነው ብለዋል።

የውሳኔ ኃሳቡ ምንም እንኳን ኢትዮጵያን ለማረጋጋትና በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ለማስፈን የሚል ስያሜ ቢሰጠውም ዋነኛ ዓላማው በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።

የውሳኔ ኃሳቡን የፃፉትና በዋናነት የደገፉት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴው ሰብሳቢ ግሬገሪ ሚክስን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦች ለሕወሃት ወገንተኝነታቸውን የሚያሳዩ መሆናቸውን አንስተዋል።

የተዘጋጀው 'ኤች አር 6600' የውሳኔ ኃሳብም ሕወሃትን ለመደገፍ የተዘጋጀ እቅድ መሆኑን ጠቁመዋል።

የውሳኔ ሀሳቡን ያሳለፉት ሰዎች ከሕወሃት ተከራካሪዎች (ሎቢስቶች) ጋር ከፍተኛ ቁርኝት እንዳላቸውና የገንዘብም ድጋፍ እንደሚደረግላቸው መረጃዎች እየወጡ መሆኑን ጠቁመዋል።

የውሳኔ ሀሳቡ የኢትዮጵያን ተጨባጭ መረጃዎች ያላማከለና ለአንድ ወገን ያደላ መሆኑን ገልጸዋል።

በውሳኔ ሀሳቡ የተካተቱት ኃሳቦች ሚዛናዊ ያልሆኑ፣ በስሜታዊነትና ከሕወሃት ጋር ባለ ወዳጅነት የተዘጋጀ መሆኑንም አስረድተዋል።

የውሳኔ ኃሳቡ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የሚያሻክር መሆኑን ጠቁመው የሚመሩት ምክር ቤትም የውሳኔ ኃሳቡን በመቃወም እንቅስቃሴ ጀምሯል ብለዋል።

ምክር ቤቱ 10 አንቀፅ ያለው የተቃውሞ ደብዳቤ አዘጋጅቶ ለሁሉም የአሜሪካ ኮንግረስና የሴኔት አባላት መላኩን ተናግረዋል።

ለ150 ሚሊዮን ሕዝብ ሊደርስ የሚችል የተቃውሞ ዝርዝር መረጃም በመገናኛ ብዙኃን እንደሚሰራጭ ገልጸዋል።

ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ አሜሪካውያን ዜጎች ምክር ቤትን የሚደግፉ 300 ሺህ ሰዎች የምክር ቤት ተጠሪዎቻቸውን ጠርተው በውሳኔ ኃሳቡ ዙሪያ እንዲያነጋግርና ተቃውሟቸውን እንዲገልጹ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።

'ኤችአር 6600' በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተጠያቂ የሚባሉ ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ መጣል፣ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ድጋፍ እንዳታደርግ ማስቆምና ከሌሎች ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እርዳታና ብድር እንዳታገኝ ክልከላ እንዲደረግ ለማስቻል የተዘጋጀ ረቂቅ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም