የደቡብ ዕዝ በተለያዩ ዘመቻዎች አኩሪ የጀግንነት ገድል እየፈጸመ ነው...ሜጀር ጄነራል ኢተፋ ራጋ

255

ሀዋሳ፤የካቲት 6/2014 (ኢዜአ) የደቡብ ዕዝ በተለያዩ ዘመቻዎች አኩሪ የጀግንነት ገድል እየፈጸመ መሆኑን በመከላከያ ሰራዊት የብሄራዊ ተጠባባቂ ኃይል ማደራጃና ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ ሜጀር ጄነራል ኢተፋ ራጋ አስታወቁ።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት ደቡብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ የላቀ የግዳጅ አፈፃፀም ላስመዘገቡና የቆይታ ጊዜያቸውን ላጠናቀቁ የሠራዊት አባላት የሜዳሊያና የማዕረግ ማልበስ መርሃ ግብር ዛሬ ተካሂዷል።

ሜጀር ጀነራል ኢተፋ ራጋ  በስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት የደቡብ እዝ የአሸባሪው ህወሀት ኃይል በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ከፈጸመበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን አኩሪ ጀግንነት እየፈጸመ  ይገኛል።

በህግ ማስከበር፣በህልውና ዘመቻና በህብረ ብሄራዊ አንድነት ዘመቻ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱ እዞች አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይ አሸባሪው ህወሓት የምስራቅ ኮሪደርን በመቆጣጠር የኢትዮጵያን ጉሮሮ ለመዝጋት ያቀደው ውጥን እንዳይሳካ በጭፍራና ሚሌ ግንባር ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ አኩሪ ጀግንነት መፈጸሙን ገልጸዋል።

ሜጀር ጀነራል ኢተፋ አክለው የደቡብ ዕዝ አመራርና የሰራዊት አባላት በአሸባሪው ህወሓት እስትንፋስ የሚንቀሳቀሰውን አሸባሪው ሸኔን  በመደምሰስ የላቀ ሚና እየተወጡ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የሀገራችንን ሠላም ለማስከበር በተሰለፉበት ግንባር ሁሉ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ለዕዙ የሠራዊት አባላት የምስጋናና የማእረግ ሽልማት መሰጠቱ ለላቀ ስራ እንደሚያነሳሳቸው ተናግረዋል።

 የደቡብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ ተወካይ ኮሎኔል ግርማ አየለ በበኩላቸው ጀግኖቹ የደቡብ ዕዝ  አባላት በተለያዩ ግንባሮች የአሸባሪ ቡድኑን አከርካሪ በመምታት በድል ላይ ድል እየተቀዳጁ ቡድኑ በአማራና አፋር ክልሎች በወረራ ይዟቸው የነበሩ አካባቢዎችን ነጻ ማውጣታቸውን ተናግረዋል።

"በተወሰደው እርምጃ ወራሪው ቡድን መሳሪያውንና ትጥቁን እያንጠባጠበ በእብሪት ወሮ ይዟቸው ከነበረው ቦታዎች ተገዶ እንዲወጣ በማድረግ ትልቅ የጀግንነት ታሪክ ተሰርቷል" ብለዋል።

በተለይ የአሸባሪው ህወሓት ቀንደኛ ደጋፊ የሆኑ አባላት በኬንያ አድርገው ወደ ትግራይ ልዩ ሃይል ሊቀላቀሉ የነበሩበትን ሁኔታ በመቀልበስ በሀገር እና በተቋሙ ላይ ሊደርስ የነበረውን አደጋ በማስቀረት በፍርድ ቤት እንዲቀጡ መደረጉን ገልጸዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥ በዕዙ የላቀ የግዳጅ አፈፃፀም ላስመዘገቡና የቆይታ ጊዜያቸውን ላጠናቀቁ  የሠራዊት አባላት  ከምክትል አስር አለቃ እስከ ሙሉ ኮሎኔል የማዕረግ እድገት መሰጠቱን አስታውቀዋል።

የኮሎኔል ማእረግ እድገት ያገኙት ዞብል ሲሳይ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የማዕረግ ዕድገቱ ብዙ ዋጋ ተከፍሎ የሚገኝ በመሆኑ ለቀጣይ ግዳጅ በተነሳሽነት እንዲሰሩ አቅም እንደሚሆናቸው ገልጸዋል።

ሌተናል ኮሎኔል ጸሐይ መንዳ በበኩላቸው የማእረግ እድገቱ ትልቅ ደስታ እንደፈጠረላቸው ገልጸው "ለቀጣይ ተልእኮ ኃላፊነቴን የበለጠ እንድወጣ አነሳስቶኛል" ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም