ባህላዊ ስፖርቶችን ለዘላቂ ሰላምና ልማት መጠቀም ይገባል-ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
ባህላዊ ስፖርቶችን ለዘላቂ ሰላምና ልማት መጠቀም ይገባል-ሚኒስቴሩ
ደብረብርሀን ፤ የካቲት 6 ቀን 2014 (ኢዜአ)ትውልዱ ባህላዊ ስፖርቶችን ለዘላቂ ሰላምና ልማት ሊጠቀምባቸው እንደሚገባ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስገነዘበ ።
19ኛው የሀገር አቀፍ የባህል ስፖርት ውድድርና 15ኛው የባህል ፌስቲቫል ዛሬ በደብረብርሀን ከተማ ተጀምሯል።
ውድድርና ፌስቲቫሉ ከየካቲት 6 እስከ 13 ድረስ የሚካሄድ መሆኑ ተመላክቷል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ ውድድርና ፌስቲቫሉን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት ባህላዊ ስፖርት በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ልዩ ትርጉም አለው ።
"ባህላዊ እሴቶቻችንን ማጎልበት ጠንካራ አገራዊ አንድነታችን ለማሳደግ የሚጠቅም በመሆኑ ወጣቶች ከአባቶቻቸው የተረከቡትን የባህል አደራ ሊጠብቁና ሊንከባከቡ ይገባል" ብለዋል ።
"የባህል ስፖርት ለአካል ብቃት ጥንካሬና ለአእምሮ እድገት ከሚሰጠው ፋይዳ በላይ የማህበረሰብ ማንነት የሚገለጥበት ሀብት ነው ዕ ሲሉም አክለዋል ።
"የኢትዮጵያን የባህል ስፖርት በዓለም አቀፍ ደረጃ በተባበሩት መንግስታትየትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (በዩኒስኮ ) እንዲመዘገብ ሚኒስቴሩ ከባህል ስፖርት ፌደሬሽን ጋር በጋራ ይሰራል" ብለዋል ።
የአማራ ክልል ባህልና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አማኑኤል ፈረደ በበኩላቸው በክልሉ በኮሮና ወረርሽኝ እና በህውሓት ወራራ ምክንያት የስፖርት እንቅስቃሴዎች ተቋርጠው መቆየቱን ተናግረዋል ።
የሽብር ቡድኑ በፈጸመው ወረራ በወልድያ ዓለም አቀፍ ስቴድየም 160 ሚሊየን ብር የሚገመት ሀብት ማውደሙን ገልጸው ዘርፉን ወደቀደመው እንቅስቃሴ ለማስገባት መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ድጋፍ እንደሚያስፈል አስታውቀዋል ።
በደብረብርሀን ከተማ ዛሬ የተጀመረው የባህል ስፖርት ውድድር በ10 ባህላዊ የስፖርት ዓይነት የሚካሄድ መሆኑን አስታውቀዋል ።
በውድድሩ የአማራ፣ የአፋር፣ የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሀዝቦች፣ የደቡብ፣ የሲዳማ፣ የኦሮሚያ፣ የቤሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችና የአደስ አባባና የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ተሳታፊ ሆነዋል ።