አትሌት በሪሁ አረጋዊ እና አትሌት ጌጤ አለማየሁ አሸናፊ የሆኑበት የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ሻምፒዮና

97

የካቲት 6/2014/ኢዜአ/ በጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በአዋቂ አትሌቶች አትሌት በሪሁ አረጋዊ እና አትሌት ጌጤ አለማየሁ አሸናፊ ሆነዋል።

39ኛው የጃንሜዳ እና 1ኛው የምስራቅ አፍሪካ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በጃንሜዳ ተካሂዷል።

ሻምፒዮናው በአዋቂ ወንድና ሴት፣ በወጣት ወንድና ሴት፣ በድብልቅ የዱላ ቅብብልና በአንጋፋ አትሌቶች መካከል ነው የተካሄደው።

በአዋቂ ወንዶች መካከል በተደረገው የ10 ኪ.ሜ ውድድር አትሌት በሪሁ አረጋዊ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ቀዳሚ ሆኖ አጠናቋል።

አንዷምላክ በልሁ ከደቡብ ፖሊስ እና አየለ ከበደ ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ሶስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።

በአዋቂ ሴቶች የ10 ኪ.ሜ ውድድር ደግሞ አትሌት ጌጤ አለማየሁ ከኦሮሚያ ክልል አንደኛ ሆና ጨርሳለች።

አትሌት  ራሄል ዳንኤል ከኤርትራ ሁለተኛ ሆና ስትጨርስ  አትሌት  እናትነሽ አላምረው ከአማራ ክልል ሶሰተኛ ሆና ወድድሯን አጠናቃለች።

በ8 ኪሜ ወጣት ወንዶች መለሰ ብርሃኑ ከአማራ ፖሊስ፣ በረከት ነጋ ከደቡብ ፖሊስ፣ ጭምዴሳ ደበሌ ከኦሮሚያ ክልል ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።

በወጣት ሴቶች የ6 ኪሎሜትር ውድድር ደግሞ ብርቱካን ወልዴ ከሲዳማ ቡና፣ መዲና ኢሣ እና አሳየች አይቼው ከአማራ ክልል እንደየቅደም ተከተላቸው ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ  ይዘው አጠናቀዋል።

May be an image of 8 people, people standing and text that says "c AF adidas SOFI MALT das SOFI MALT EAF adidas SOFI MALT FAF adidas SOFI MALT EAF adidas SOF MALT AF ad AF adidas SOFI MALT EAF adidas SOFI MALT EAF EAF adidas SOFI MALT didas SOFI MALT FF ALT FI AF FF adidas SOFI MALT FZF adidas S EAF FAF lida FI FI LT F adid OFIEA adidas 1F"

በውድድሩ በአዋቂ ወንድና ሴት አንደኛ የወጡ አትሌቶች እያንዳንዳቸው 50 ሺህ ብር፣ ከሁለተኛ እስከ ስድስተኛ ሆነው ያጠናቀቁ ደግሞ እንደቅደም ተከተላቸው 25 ሺህ ብር፣ 20 ሺህ ብር፣ 18 ሺህ ብር፣ 16 ሺህ ብር እና 14 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆነዋል።

በወጣት ወንድና ሴት ውድድር ቀዳሚ ሆነው የጨረሱ አትሌቶች የ40 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆነዋል።

ከሁለተኛ እስከ ስድስተኛ ደረጃ የወጡ አትሌቶች 20 ሺህ፣ 16 ሺህ፣ 14 ሺህ፣ 12 ሺህ እና 10 ሺህ ብር  ተሸልመዋል።

በሌሎች የውድድር ዘርፎች ለተካፈሉና ላሸነፉ አትሌቶችም የገንዘብና የሜዳሊያ ሽልማት ተሰጥቷል።

የኢትዮጵየ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተሳትፎና ውድድር ንዑስ የስራ ሂደት መሪ አቶ አስፋው ዳኜ በዚህ ውድድር በአትሌቶች መካከል ከፍተኛ ፉክክር እንደነበር ገልጸዋል።

በርካታ ወጣት አትሌቶች ያላቸውን አቅም ያሳዩበት ሻምፒዮና እንደሆነም ነው የተናገሩት።

በዚህ ሻምፒዮና ለመሳተፍ ማረጋጋጫ የሰጡት ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ኬንያና ታንዛኒያ  አትሌቶቻቸውን ልከው በሩጫው መሳተፋቸውን አቶ አስፋው ጨምረው ገልጸዋል።

በወጣቶች መካከል በተደረገው ውድድር በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚደረጉ ሌሎች ሀገራት የገንዘብ ሽልማት የማይሰጥ ቢሆንም በጃንሜዳ ውድድር ግን ወጣቶችን ለማበረታታት በሚል የገንዘብ ሽልማት መሰጠቱንም ገልጸዋል።

ፌዴሬሽኑ ለአሸናፊ አትሌቶች ለሽልማት ብቻ ከ800 ሺህ ብር በላይ ወጪ ማድረጉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም