ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የግማሽ ማራቶን ውድድር ዛሬ በሐዋሳ ከተማ ተካሄደ

93

ሀዋሳ የካቲት 06/2014 (ኢዜአ) ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በሃዋሳ ከተማ ዛሬ የግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር አካሄዷል፡፡

በግማሽ ማራቶን ውድድሩ በሁለቱም ጾታ ከአዲስ አበባ የተሳተፉ የግል ተወዳዳሪዎች ያሸነፉ ሲሆን አንደኛ ለወጡ አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው የ25 ሺህ ብር ፣ የሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል ፡፡

በወንዶች በተደረገው ውድድር አትሌት  ባዘዘው አስማረ አንደኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ጌታቸው ኬኔ እና እዝቅያስ ምስጋናው ሁለተኛና ሶስተኛ በመሆን  አጠናቀዋል ፡፡

በሴቶች በተደረገ ተመሳሳይ ውድድር አትሌት ጥሩዬ መስፍን አንደኛ ስትወጣ መልካም ዋሌና ያለምጌጥ ያረጋል ሁለተኛና ሶስተኛ በመሆን ውድድሩን አሸንፈዋል ፡፡

በወንዶች ውድድሩን አንደኛ በመውጣት ያሸነፈው አትሌት ባዘዘው አስማረ በሀዋሳ ከተማ በተደረገው የግማሽ ማራቶን ውድድር ለመጀመሪያው ጊዜ መሳተፉንና በማሸነፉ ደስተኛ እንደሆነ  ተናግሯል ፡፡

መሰል ውድድሮቹ  ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ሚናቸው ከፍተኛ በመሆኑ በተለያዩ ከተሞች ተጠናክሮ ሊቀጥሉ ይገባል ሲል ጠቁሟል ፡፡

በሴቶች የተደረገውን ውድድር ያሸነፈችው አትሌት ጥሩዬ መስፍን በበኩሏ የሀዋሳ ከተማ ለእንደዚህ አይነት ውድድሮች ምቹ በመሆኗ ለማሸነፍም እንደረዳት ተናግራለች ፡፡

ከተሳታፊ ተወዳዳሪዎች መካከል የሐዋሳ ነዋሪ አቶ ነቢል መሀመድ ቤተሰቦቻቸውን ጭምር ይዘው የተሳተፉ ሲሆን አስደሳች ጊዜ ማሳለፋቸውን ተናግረዋል ፡፡

ከፉክክር ባሻገር ኢትዮጵያዊ አብሮነታችንን ያሳየንበት ውድድር ነው ያሉት አቶ ነቢል ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር ስፖርታው እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ በመሆኑ በየወቅቱ ቢካሄድ ጠቃሚ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዝግጅቱ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ከተማዋ በኢንቨስትመንና በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ተፈላጊነቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው የጎዳና ላይ ስፖርታዊ  ውድድሮች መካሄዱ ተመራጭነቷን ይበልጥ እንደሚያጎላው ገልጸዋል ፡፡

አስተዳደሩ በቀጣይም መሰል ውድድሮችን በማካሄድ ከተማዋን በስፖርት ቱሪዝም ዘርፍ ለማስተዋወቅ ወደ ተግባር  መግባቱን  ጠቁመዋል ፡፡

ውድድሩ በሀዋሳ ሲካሄድ ለ10ኛ ጊዜ እንደሆነ የገለጹት የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ማርኬትንግ ዳይሬክተር ወይዘሪት ህሊና ንጉሴ በበኩላቸው አምና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ሳይካሄድ መቅረቱን አስታውሰዋል ፡፡

ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ የተደረገው የግማሽ ማራቶን ውድድር እጅግ ደማቅ እንደሆነም ገልጸዋል ፡፡

በውድድሩ ባጠቃላይ ከሁለት ሺህ 800 ሰዎች በላይ መሳተፋቸውንና 250 የሚሆኑ አትሌቶች እንደተገኙበት አስታውቀዋል ፡፡

በአዲስ አበባም ሆነ በክልል ከተሞች የሚካሄዱ የታላቁ ሩጫ ውድድሮች ለቱሪዝም ዘርፉና ለኢኮኖሚ መነቃቃት የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ የጎላ  መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህ ውድድር  ከ500 በላይ ዜጎች በተሳታፊና በአስተባባሪነት ከአዲስ አበባ ወደ ሀዋሳ ከተማ መጓዛቸውን ጠቁመው ይህም የእርስ በእርስ ግንኙነቱን ለማጠናከር የላቀ ሚና እንዳለው ነው የተናገሩት ፡፡

በግማሽ ማራቶን ውድድሩ አንደኛ የወጡት አትሌቶች እያንዳንዳቸው የ25 ሺህ ብር ፣ የሜዳሊያና ዋንጫ ተሸላሚ ሲሆኑ በአጠቃላይ ለሽልማት 100 ሺህ ብር ወጪ እንደተደረገ ወይዘሮ ህሊና ጠቁመዋል ፡፡

ከግማሽ ማራቶን ውድድሩ በተጨማሪ የ5 ኪሎ ሜትር የአዋቂዎችና የ3 ኪሎ ሜትር የሕፃናት ውድድሮች ተካሂዷል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም