ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል በማስመዝገብ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ ባለሃብቶች ወደ ስራ እየገቡ ነው

48

እንጅባራ የካቲት6/2014 (ኢዜአ) በአዊ ብሔረሰብ ዞን ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 53 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ በመውሰድ ወደ ልማት እየገቡ መሆኑ ተገለጸ።

በአዊ ብሔረሰብ ዞን የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ተወካይ ኃላፊ አቶ አበራ ገበየሁ ለኢዜአ እንዳሉት በዞኑ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ እድገት በትኩረት እየተሰራ ነው።

በዞኑ ባለፉት 6 ወራት በጨርቃጨርቅ፣ በእንጨትና ብረታ ብረት፣ በኬሚካል፣ በአግሮ-ፕሮሰሲንግ እና በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት ላቀረቡ  ባለሀብቶች ፈቃድ መሰጠቱን ገልፀዋል።

ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ካስመዘገቡ 53 ባለሃብቶች መካከል   35ቱ በማኑፋክቸሪንግ፣ 13ቱ በአግሮ-ፕሮሰሲንግ ፣ 5ቱ  በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፎች ለመሰማራት ፈቃድ መውሰዳቸውን  አቶ አበራ ተናግረዋል።

በኢንቨስትመንት ዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ከ34 ነጥብ 7 ሄክታር በላይ መሬት መዘጋጀቱንና እስካሁን 8 ባለሃብቶች  ቦታ ተረክበው ወደ ግንባታ መግባታቸውን ጠቅሰዋል።

ባለሃብቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገቡ ከ10 ሺህ ለሚበልጡ ወገኖች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የጠቀሱት።

ከዚህ ጎን ለጎንም በተካሄደ ህግ ማስከበር ስራ ቦታ ተረክበው ወደ ልማት ካልገቡ ዘጠኝ ፕሮጀክቶች መሬት የመንጠቅ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።

በእንጅባራ ከተማ የቢሮ ዕቃዎችንና የግንባታ ምርቶችን ለማምረት 500 ካሬ ሜትር ቦታ ተረክበው ወደ ግንባታ መግባታቸውን  የገለፁት ደግሞ አቶ አጉማስ አረጋ የተባሉ ባለሃብት ናቸው።

ግንባታውን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ወደ ማምረት ስራ እንደሚገቡ አቶ አጉማስ  ተናግረዋል።

በብሔረሰብ አስተዳደሩ ዞኑ  ከ141 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የተገነቡ 344 የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች እንዳሉ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም