ትክክለኛ መረጃን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን መከላከል ይገባል

64

የካቲት 6/2014/ኢዜአ/ ትክክለኛ መረጃን በፍጥነት ለኅብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን መከላከል እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ሬድዮ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ዓለም አቀፉ የሬዲዮ ቀንን ዛሬ አክብሯል።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ በዚህ ጊዜ እንደገለጹት፤ በማኅበራዊ ሚዲያዎች  የሚተላለፉ ሐሰተኛ መረጃዎች በሕዝቡ ሰላም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠሩ ነው።   

በተለይም አሁን ላይ በማኅበራዊ ሚዲያን የተለያዩ ቡድኖች የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ሌሎች ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም ሐሰተኛ መረጃዎች እያሰራጩ መሆኑን ተናግረዋል።

የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን በሕግ ማዕቀፍ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ከዚህ ጎን ለጎን ኅብረተሰቡም መረጃን ከትክክኛ ምንጭ መጠቀም እንዳለበት ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡም ሐሰተኛ መረጃዎችን ባለመጠቀምና ባለማጋራት ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል።

በተለይም ደግሞ መገናኛ ብዙኃን ተቋማት ትክክለኛ መረጃን በፍጥነት ለኅብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን መከላከል እንደሚጠበቅባቸውም ነው ያሳሰቡት።

በዚህ ረገድ ሬድዮ ኅብረተሰቡን በማንቃትና ትክክለኛ መረጃን ተደራሽ በማድረግ በኩል ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በአማራ ክልል የሚገኙ 3 የማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን መውደማቸውን ጠቅሰው፤የሬዲዮ ጣቢያዎቹን ወደ አገልግሎት ለመመለስ ኅብረተሰቡ በመልሶ ግንባታው ሊረባረብ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

ከዚህ አኳያ ባለሥልጣኑ የአቅም ግንባታ ድጋፍ እንደሚያደርግና ሌሎችም ድጋፍ እንዲያደርጉ እንደሚያስተባብር አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚና የሬዲዮ ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ሃቢባ ፋሪስ በበኩላቸው ሬድዮ ለበርካታ ማኅበረሰቦች ተደራሽ የሆነ መገናኛ ብዙሃን አማራጭ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ይህንን በርካታ ጠቀሜታ ያለው የመገናኛ ብዙሃን አማራጭ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመደገፍ ይበልጥ ለማዘመን እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የሬዲዮ ቀን መከበሩም የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትን የእርስ በእርስ ግንኙነት ለማጠናከር ያስችላል ነው ያሉት።   

ዓለም አቀፍ የሬዲዮ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ11ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ3ኛ ጊዜ ነው የተከበረው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም