አንጋፋው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያስገነባው አዲስ ህንጻ ዛሬ ይመረቃል

የካቲት 6 ቀን 2014 (ኢዜአ) 80 ወርቃማ ዓመታትን ያስቆጠረው አንጋፋው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያስገነባው አዲስ ህንጻ በዛሬው እለት ይመረቃል።

በኢትዮጵያ 117 ዓመታትን ያልበለጠ እድሜ ባስቆጠረው የባንክ ስራ ታሪክ ትልቅ አሻራ ይዞ የዘለቀ የፋይናንስ ተቋም ነው፤የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ።

በ1935 ዓ.ም በ1 ሚሊዮን የማሪያትሬዛ መነሻ ካፒታል ‘የኢትዮጵያ መንግስት ባንክ’ በሚል የብሔራዊ ባንክን እና የንግድ ባንክን ሚና አጣምሮ በመያዝ ነበር የተመሰረተው።

በ1955 ዓ.ም ብሔራዊ ባንክ ሲቋቋም ‘የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ’ በሚል ስያሜ የአገሪቷን ገንዘብ ተቆጣጣሪነት ሚናውን በመተው በንግድ ሥራ ዘርፉን ይዞ ቀጠለ።

80 ዓመታትን ያስቆጠረው ይህ አንጋፋ ባንክ በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ ከ1 ሺህ 800 በላይ ቅርንጫፎች እና ከ34 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን አፍርቷል።

80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ሲያከብር ግን በአገሪቱ ብቻ ሳይሆን በቀጣናው ሰማይ ታካኪ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት ህንፃ ገንብቶ በዛሬው እለት ያስመርቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም