የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ቁሳቁስ ለደሴ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ድጋፍ አደረገ

116

ደሴ፣ የካቲት 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ በክልሉ ያሉ አራት የጤና ሳይንስ ኮሌጆችን በማስተባበር ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ቁሳቁስ ለደሴ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ድጋፍ አድርጓል፡፡

ቢሮው አሸባሪው ህወሃት ወረራ በፈጸመበት ወቅት ውድመትና ዝርፊያ ፈጽሞ ከአገልግሎት ውጪ ያደረጋቸውን የጤና ተቋማትን መልሶ በማደራጀት አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ዶክተር ጋሹ ክንዱ፤ አሸባሪ ቡድኑ በክልሉ 40 ሆስፒታሎች፣ 453 ጤና ጣቢያና 1 ሺህ 850 ጤና ኬላዎችን መዝረፉንና ማውደሙን ጠቅሰዋል፡፡

"የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱን ጠብቆ በመረዳዳት፣ በመተባበርና በመተጋገዝ ባህሉ ተቋሞችን መልሶ እያቋቋመ በመሆኑ ተቋሟቱን ደረጃ በደረጃ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ነው" ብለዋል።

ከጉዳቱ ስፋት አንጻር ለድንገተኛ፣ ለወላድ እናቶችና ጊዜ ለማይሰጡ ተመላላሽ ህመምተኞች ብቻ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው፤ ተቋማቱ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ ሁሉም የአቅሙን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የጎንደር ጠዳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን አቶ ዘመነ ሀብቱ በበኩላቸው "ካለን ቀንሰን የተለያየ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋችን አንድነታችንና የእርስ በርስ ግንኙነታችን ለማጠናከር ያግዘናል" ብለዋል፡፡

''የሽብር ቡድኑ ኮሌጁን ንብረት ሙሉ በሙሉ ከመዝረፉ ባለፈ ቀሪውም ተጠግኖ አገልግሎት እንዳይሰጥ ባለበት ማውደሙን'' የገለፁት ደግሞ የደሴ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አካዳሚክ ምክትል ዲን አቶ አንዳርጌ ስመኝ ናቸው።

ኮሌጁን በማቋቋም ከየካቲት 07 ቀን 2014 ዓም ጀምሮ የመማር ማስተማር ስራውን ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ለተማሪዎች ጥሪ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም