ኢትዮጵያን በተመለከተ የተዘጋጀው ረቂቅ ሕግ እንዳይጸድቅ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገለጸ

44

የካቲት 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን በተመለከተ በዴሞክራትና የሪፐብሊካን ፓርቲ የኮንግረስ አባላት የተዘጋጀው ረቂቅ ሕግ እንዳይጸድቅ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን የኢትዮ አሜሪካውያን የእድገት ምክር ቤት አስታወቀ።

በአሜሪካ የኮንግረስ አባላት ቶም ማሊኖውስኪ (ኒው ጀርሲ)፣ ያንግ ኪም (ካሊፎርኒያ)፣ ግሪጎሪ ሚክስ (ኒው ዮርክ) እና ማይክል ማካውል (ቴክሳስ) 'ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት' ወይም ኤችአር 6600 በሚል ያዘጋጁት ረቂቅ ሕግ ከሰሞኑ በኮንግረሱ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ውይይት እንደተደረገበት ይታወቃል።

ኤችአር 6600 በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ጦርነት ተጠያቂ ናቸው ያላቸው ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ መጣል፣ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን የደህንነትና የንግድ ድጋፍ እንድታቆምና ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እርዳታና ብድር እንዳታገኝ ክልከላ እንዲደረግ ማስቻል የሚሉ ሀሳቦችን የያዘ ረቂቅ ሕግ ነው።

የኢትዮ አሜሪካውያን የእድገት ምክር ቤት ረቂቅ ሕጉ እንዳይጸድቅ የሚያስችል እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመሩን ገልጿል።

በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ሕጉን የሚቃወምና እንዳይጸደቅ የሚያሳስብ ደብዳቤ ለአሜሪካ ኮንግረስ ማስገባታቸውንና ይሄ ሂደት አሁንም እንደቀጠለ አመልክቷል።

እስካሁን ከ435 የኮንግረስ አባላት 149ኙ እንዲሁም ከ100 የሴኔት አባላት 64ቱን በማግኘት ኤችአር 6600 ረቂቅ ሕግን አስመልክቶ ያለውን ሁኔታ እንዲያውቁት መደረጉን ምክር ቤቱ አስታውቋል።

ረቂቅ ሕጉ እንዳይጸድቅ የተጀመረው እንቅስቃሴ በተጠናከረ መልኩ መቀጠል እንዳለበትና ለዚህም በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን በየአካባቢያቸው የሚገኙ የኮንግረስና የሴኔት አባላት በማነጋገር ያለውን እውነታ ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል ብሏል።

ኤችአር 6600 ለረጅም ጊዜ የቆየውን የኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙንት የሚጎዳና ያለውን ነባራዊ እውነት ያልተረዳ መሆኑን 'የአሜሪካ ኢትዮጵያውያን ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ' የተሰኘው ተቋም መግለጹ የሚታወቅ ነው።

ረቂቅ ሕጉ እንዳይጸድቅ የተደራጀ እንቅስቃሴ በማድረግ ለኢትዮጵያ ድምጽ እንሁን ሲልም ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም