ድርጅቱ በ10 ሚሊዮን ብር ወጪ በሎጊያ ከተማ የትምህርት ቤት ማስፋፊያ ግንባታ ሊያካሂድ ነው

79

ሰመራ፣ የካቲት 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) ግሎባል አሊያንስ ግብረ ሰናይ ድርጅት በ10 ሚሊዮን ብር ወጪ በአፋር ክልል ሎጊያ ከተማ የትምህርት ቤት ማስፋፊያ ግንባታ ሊያካሂድ መሆኑ ተገለጸ።

ድርጅቱ በሎጊያ አንደኛ  ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ የማስፋፊያ ግንባታ ለመጀመር ትናንት የመሰረተ ድንጋይ አስቀምጧል።

እስከ 7ኛ ክፍል ድረስ የሚያስተምረው የሎጊያ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት  ርዕሰ መምህር ወይዘሮ ህይወት ሽመልስ በስነሰርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ ትምህርት ቤቱ በአንድ ክፍል እስከ 120 ተማሪዎች በተጨናነቀ ሁኔታ እያስተማረ ይገኛል።

ትምህርት ቤቱ የመማሪያና አስተዳደር ክፍሎች ጥበት በተጨማሪ የውሃና የመጸዳጃ ቤት ችግሮች ያሉበት መሆኑን ጠቁመው፤ ይህ ችግር ተማሪ የመቀበል አቅሙን እንደገደበበት ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ትውልድ ለመቅረጽ የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ ነው ያለው የግሎባል አሊያንስ ቦርድ ሰብሳቢ አርቲስት ታማኝ በየነ፤ የትምህርት ቤቱን ችግሮች ለመፍታት የድርጅቱን አባላት በማስተባበር በቀጣይ ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግሯል።

ግንባታው  እስከ 10 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚፈጅና ስራው በአፋር ልማት ማህበር በኩል የሚከናወን መሆኑን ጠቅሷል።

የአፋር ክልል ህዝብ ለሀገሩ ያለውን ዘመን የማይሽረው ታማኝነት በተግባር አስተምሮናል ሲል አርቲስት ታማኝ ገልጿል።

"በውጭ  የምትኖሩ ወንድሞቼና እህቶቼ ወገናችሁ ለሀገሩ እየከፈለ ያለውን መስዋእትነት በመረዳት በምንችለው ሁሉ ከአፋር ህዝብ ጎን  ልንቆም ይገባል" ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።

የአፋር ልማት ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ኑረዲን ሰዲቅ በበኩላቸው "ግሎባል አሊያንስና አርቲስት ታማኝ በየነ ከአፋር ህዝብ ጎን በመቆም እያደረገ ያለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ የሚደነቅ ነው" ብለዋል

በግብረሰናይ ድርጅቱ የገንዘብ ድጋፍ የሚገነባው የትምህርት ቤት ማስፋፊያ  8 የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ባለሁለት ብሎክና የአስተዳደር ህንጻን ጨምሮ ሌሎች ግንባታዎችን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰው፤ ግንባታው በ8 ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም