ሥራ ፈጣሪዎችን ከባለኃብቶች ጋር የሚያገናኝ "ስሙኒ" የተሰኘ መተግበሪያ ይፋ ሆነ

115

የካቲት 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪዎችን ከባለኃብቶች ጋር የሚያገናኝ "ስሙኒ" የተሰኘ መተግበሪያ ይፋ ሆነ ።

መተግበሪያው ባለኃብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት መነሻ ኃሳቦች ማግኘት ያስችላቸዋል ተብሏል።

ባለኃብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ በማስቻል የውጭ ኢንቨስትመንትን ጭምር በመሳብ ለምጣኔ ኃብት እድገቱ ጉልህ ሚና ይጫወታል ተብሏል።

የስሙኒ መተግበሪያ ከኮካ ኮላ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በዓመት 10 የሚጠጉ ጀማሪዎችን የ100 ሺህ ብር የገንዘብ ፈንድ እንደሚደግፍ ተጠቁሟል።

ስሙኒ የሥራ ፈጣሪዎችና ባለኃብቶችን በማገናኘት የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት እድገት በቀላሉ ለመገንባትና ለመጠቀም የሚያስችል የኦን ላይን መድረክ መሆኑም ተመላክቷል።

በሥራና ክህሎት ሚንስቴር የአጋርነትና ፈንድ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ጥኡመእግዚ በርሄ፤ሚነስቴር መሥሪያ ቤቱ ወጣቶች የሥራ እድል እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እየሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም ወጣቶች በክህሎት ብቁ እንዲሆኑ እና ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው ከሥራ አጥነት እንዲላቀቁ ከተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት ጋር አጋርነት በመፍጠር የተጣለበትን ኃላፊነት እየተወጣ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

መንግሥት ከግሉ ሴክተሩ ጋር እየሰራ መሆኑንና የሕግ ማዕቀፎችን በማሻሻል የግሉ ሴክተሩ ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወት እያበረታታ መሆኑንም አክለዋል።

አሁን ያሉ ወጣቶችም እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች በመመልከት የተሻሉ ሥራዎችን ሊሰሩ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የመተግበሪያው ባለቤት ወጣት ብሩክ ግርማ፤ መተግበሪያውን ሰርቶ ለማጠናቀቅ ሦስት ዓመታትን እንደፈጀና አንድ ሚልየን ብር ገደማ ወጭ እንደተደረገበት ጠቁመዋል።

መተግበሪያው ባለሀብቶች አገልግሎት ሰጭዎችን እንዲሁም ሥራ ፈላጊዎች በአንድ መድረክ ላይ የሚያገናኝ መሆኑን ገልጿል።

የስሙኒ መተግበሪያን ተጠቃሚዎች ከፕሌይ ስቶር በማውረድ መገልገል ይችላሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም