ለአፍሪካ አንድ ጠንካራ ሚዲያ መኖር የምዕራባዊያኑን ሴራ ለማጋለጥ ያግዛል

97

ጂንካ ፤የካቲት 3/2014(ኢዜአ) ለአፍሪካ አንድ ጠንካራ ሚዲያ መኖር የምዕራባዊያኑን ሴራ ለማጋለጥና የአህጉሩን እውነት ለአለም ህዝብ ለማሳወቅ እንደሚያግዝ አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ።

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል የጂንካ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት እና ተግባቦት መምህር ሀይሬዲን ሙሐመድ ለኢዜአ እንዳሉት፤በአፍሪካ ህብረት የሚመራ ፈርጠም ያለ ሚዲያ መቋቋሙ የምዕራባውያን ሚዲያዎችን ለመሞገት አቅምም፤ ተደማጭነትም ይኖረዋል።

አረብ ሀገራት እንደ "አልጄዚራ" ፤ ቻይና ደግሞ "ሲጂቲኤን"   የመሠረቱት የምዕራባውያን ሀገራትን ተፅእኖ ለመቋቋም መሆኑን አንስተዋል።

ለአፍሪካም አንድ ጠንካራ ሚዲያ መኖር እውነታውን ለአለም ህዝብ ለማሳወቅና የምዕራባዊያኑን ሴራ ለማጋለጥ ያግዛል ብለዋል።

የሚቋቋመው ሚዲያም አፍሪካ በረሃብ፣በጦርነት፣በኋላ ቀርነት እና በምዕራባዊውያን እርዳታ የምትኖር አህጉር ተደርጋ የተሳለችበት ምስልን በበጎ ገፅታ የመለወጥ አቅም እንደሚኖረው ምሁሩ አስረድተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የቀረበው በአፍሪካ ጠንካራ አህጉራዊ ሚዲያ የማቋቋም ሀሳብ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያለው መሆኑን በመገንዘብ በተለይም የአፍሪካውያን መሪዎች ለተፈጻሚነቱ በልዩ ትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ አፍሪካ አህጉራዊ ሚዲያ ያስፈልጋታል ብለው ያቀረቡት ሀሳብ ተገቢ ነው ያለው ደግሞ የደቡብ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ጂንካ ቅርንጫፍ ጋዜጠኛ ዳኜ ጥላሁን ነው።

ይህም አፍሪካዊያንን የሚያቀራርብ እና ወደ አንድነት የሚያመጣ ሀሳብ እንዲሁም የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤንና ንቅናቄው  ለማጠናከር ተጨማሪ አቅም ይሆናል ብሏል።

አፍሪካ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ያላት፣የሰው ዘር መገኛና የበርካታ ባህላዊ እሴቶች ባለቤት ብትሆንም በምዕራባዊያን ሚዲያዎች የተሳለችው ጽንፍ የያዘ አተያይ ለመቀየር እንደሚያግዝ ተናግሯል።

ይህ ሀሳብ በተፈለገው ፍጥነት ተግባራዊ እንዲሆን መሪዎች በተቀናጀ መልኩ ጥረት ሊያደርጉ ይገባል ነው ያለው ጋዜጠኛ ዳኜ።

የደቡብ ኦሞ ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን የዲጂታል ሚዲያ ዳይሬክተር አቶ ኤሳው በርሻ  በበኩላቸው፤ አፍሪካ የምዕራባዊያን ሀገራት ፍላጎት ማስፈፀሚያ ከመሆን በራስ መተማመን ላይ የተመሰረተ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ጊዜው አሁን መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ ለረጀም ዘመናት የዘሩትንና በተለያየ አጀንዳ ለመከፋፈል የሚያደርጉትን የምዕራባውያንን ስውር ፍላጎት  የሚያጋልጥና ለአፍሪካውያን ጥብቅና በመቆም የሚሞግት ጠንካራ አህጉራዊ ሚዲያ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በህብረቱ ጉባኤ ላይ ያቀረቡት ሀሳብ በአፍሪካዊያን ላይ የሚደረገውን ጫና ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው ብለዋል።

የሚቋቋመውም ሚዲያ  የአፍሪካ ምሁራን በአህጉራዊ ጉዳዩች በቅርበት እንዲመክሩና ለአህጉሩ  ዕድገት የሚጠቅሙ ሀሳቦችን እንዲያመነጩ ያግዛልም ነው ያሉት ።

የአፍሪካዊያንን በተደራጀ መልኩ በዓለም አደባባይ ጥቅማቸውን እንዲያስከብሩ ከፍተኛ አቅም እንደሚሆን ጠቅሰው፤  ይህ ሀሳብ ተፈጻሚ እንዲሆን አፍሪካዊያን መሪዎች በጠንካራ አቋም ሊመሩትና ሊተገብሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሄደው 35ኛው የህብረቱ  የመሪዎች ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ  "የአፍሪካ ድምጽ የሚሰማበት፣ የፓን አፍሪካዊነት ድምጽ የሚንጸባረቅበት የጋራ አህጉራዊ ሚዲያ ሊኖረን ይገባል" ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ የ"ግሎባል ቴሌቪዥን ኔትወርክ ኦፍ አፍሪካ" መስራችና የቻይና ዓለም አቀፍ ቴሌቭዥን ኔትወርክ (ሲጂቲኤን) ዘጋቢ ግሩም ጫላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት ሃሳብ ወቅታዊና ትክክለኛ መሆኑን ለኢዜአ መናገሩ ተዘግቧል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ መገናኛ ብዙሃን የጦርነት ሜዳ እየሆኑ በመምጣታቸው ጉዳዩ ጊዜ ሊሰጠውና  አፍሪካም የራሷን ተጽእኖ ፈጣሪ ሚዲያ በማቋቋም ጥቅሟን ማስከበር እንደሚገባ ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም