ህገ ወጥ 397 ሽጉጦችና አንድ ክላሽንኮቭ ጠብመንጃ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አሰታወቀ

64

መተማ/ እንጅባራ፤ የካቲት 3/2014 (ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ በህገ ወጥ መንገድ የተገኙ 397 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥና አንድ ክላሽንኮቭ ጠብመንጃ ከተተኳሽ ጥይቶች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር ሀይሌ ብርሃኑ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በወረዳው ጠረፍ ወርቅ ከተማ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ ነው።

በጥቆማው መሰረት ትናንት ማምሻውን በከተማዋ አንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ  በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ  ከተገኙት ሽጉጦቹና ጠብመንጃው ሌላ  60 ተተኳሽ የክላሽ ጥይቶችና 13 የክላሽንኮቭ ሰደፍ  በማዳበሪያ በመጠቅለል ተደብቀው ማግኘት መቻሉን ገልጸዋል።

በወንጀሉ የተጠረጠረው የቤቱ ባለቤት   ለጊዜው ባይያዝም፤ በቁጥጥር ስር ለማዋል የፀጥታ ሃይሉ በተቀናጀ አግባብ ክትትል እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

ሆኖም የጸጥታ አካላት የተጠረጠሪውን ቤት ለመበርበር ሲያመሩ በእንግድነት ለማደር የተገኙ አራት ሰዎች ቤቱን ላለማስፈተሽ ጥረት በማድረጋቸው  በወንጀሉ  ተሳትፎ ሊኖራቸው ይችላል በሚል በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ረዳት ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ የፀጥታ ስጋት የሆነውን የህገ ወጥ መሳሪያ ዝውውር ለመከላከል የፀጥታ ሃይሉን ጥረት በማገዝ ላደረገው ጥቆማ ምስጋና አቅርበዋል።

ዘላቂ ሰላም ሊመጣ የሚችልው የፀጥታ ሃይሉ ከአካበቢው ማህበረሰብ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ሲሰራ እንደሆነ አመልክተው፤ ህብረተሰቡ አሁንም መሰል አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥመው በመጠቆም የህግ የበላይነትን እንዲያረጋግጥ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር እንጅባራ ከተማ  ኬላ ላይ በተደረገ ፍተሻ በሁለት የህዝብ ማመላሻ ተሽከርካሪዎች ሲዘዋወር የተገኘ 1 ሺህ 125 ተተኳሽ ጥይቶች ዛሬ  በቁጥጥር ስር መዋሉን የከተማዋ አስተዳደር ፖሊስ ጽህፈት ቤት  ኃላፊ ኮማንደር አበበ ዘውዴ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ከዚህ ውስጥ በሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3- 24081 አማ  "ሃይሩፍ"  የህዝብ ማመላለሻ  ተሽከርካሪ የተገኘው ጥይት ከነተጠርጣሪው እጅ ከፍንጅ በፖሊስ ተይዞ   በአፋጣኝ ፍርድ ቤት አምስት ዓመት እስራትና  500 ብር ቅጣት እንደተወሰነበት አስታውቀዋል።

በሌላው የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ   ህገ ወጥ ተተኳሽ ጥይት የተገኘበት  ተጠርጣሪ ለጊዜው ቢያመልጥም አሽከርካሪው በቁጥጥር ሥር ውሎ ወንጀሉ እየተጣራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም