በ39ኛው የጃንሜዳ እና 1ኛው የምስራቅ አፍሪካ አገር አቋራጭ ውድድር የአምስት አገራት አትሌቶች ይሳተፋሉ

193

የካቲት 3/2014/ኢዜአ/ የፊታችን እሁድ በሚካሄደው 39ኛው የጃንሜዳ እና 1ኛው የምስራቅ አፍሪካ አገር አቋራጭ ውድድር የአምስት አገራት አትሌቶች የሚሳተፉ መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ገለጸ።

የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገዛኸኝ አበራ፤ ውድድሩን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ አምስት አገራት አትሌቶቻቸውን በውደድሩ ለማሳተፍ ማረጋገጫ መስጠታቸውን ገልጿል።

ውድድሩ ለአገር ገፅታ ግንባታም አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግሮ ከሌሎች ዓመታት ከፍ ያለ ሽልማት መዘጋጀቱን ተናግሯል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ረዳት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሃንስ እንግዳ፤ በውድድሩ አትሌቶች አቋማቸውን የሚፈትሹበት ነው ብለዋል።  

ውድድሩ በአምስት ካታጎሪ ማለትም በአዋቂ ወንድና ሴት በወጣት ወንድና ሴትና በድብልቅ የዱላ ቅብብል ውድድሩ ይካሄዳል ተብሏል።

ከዚህ በተጨማሪ የአንጋፋ አትሌቶች ውድድር እንደሚካሄድም ተጠቁሟል።

በውድድሩ በአዋቂ ወንድና ሴት አንደኛ ለሚወጡ ለእያንዳንዳቸው 50 ሺህ ብር፣ ከሁለተኛ እስከ  ስድስተኛ ሆነው ለሚያጠናቅቁ 25 ሺህ ብር፣ 20 ሺህ ብር፣ 18 ሺህ ብር፣ 16 ሺህ ብር፣ 14 ሺህ ብር እንደየቅደም ተከተላቸው ተሸላሚ ይሆናሉ።

በወጣት ወንድና ሴት ደግሞ አንደኛ ሆነው ለሚያጠናቅቁ እያንዳንዳቸው 40 ሺህ ብር ይሸለማሉ።

ከሁለተኛ እስከ ስድስተኛ ለሚወጡ 20 ሺህ ብር፣ 16 ሺህ ብር፣14 ሺህ ብር፣ 12 ሺህ እና 10 ሺህ ብር ሽልማት ያገኛሉ ተብሏል።

አሁድ የካቲት 6 ቀን 2014 ዓ.ም በጃንሜዳ በሚካሄደው ውድድር 473 ወንድ እና 251 ሴት አትሌቶች እንደሚካፈሉ ተገልጿል።

በውድድሩ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የኬኒያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ታንዛኒያ አገራት አትሌቶች ይሳተፋሉ።