የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት የሚያስችል የገቢ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር ተጀመረ

348

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 3/2014 (ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሃት የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት በአጭር የፅሁፍ መልእክትና በባንክ አካውንት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ተጀመረ።

ትምህርት ሚኒስቴር ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በአሸባሪው ሕወሃት ውድመት የደረሰባቸውን የትምህርት ተቋማት መልሶ ለመገንባት የሚያስችለውን የገቢ ማሰባስቢያ በተመለከተ የጋራ ሥምምነት አድርገዋል።

የገቢ ማሰባሰቢያው “ኑ የወደመውን የትውልድ ማረፊያ ተቋም አብረን እንገንባ” በሚል መሪ ኃሳብ የሚካሄድ እንደሆነ ተገልጿል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ አሸባሪው ሕወሃት በአማራና አፋር ክልሎች በወረራ በቆየባቸው አጋጣሚዎች በድምሩ 1 ሺህ 90 የትምህርት ተቋማት ሙሉ በሙሉ ሲወድሙ ሶስት ዩኒቨርሲቲዎችና ሶስት ኮሌጆችም ተመሳሳይ እጣ ገጥሟቸዋል ብለዋል።

እነዚህን ትምሀርት ቤቶች መልሶ በመገንባት ከትምህርት ገበታቸው የራቁትን የነገ አገር ተረካቢ ትውልዶች ወደ ትምህርት እንዲመለሱ ለማድረግ በጋራ ርብርብ ማድረግ ይገባል ብለዋል።  

በመሆኑም የትምህርት ተቋማቱን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ሁሉም ከገንዘብ ድጋፉ በተጨማሪ የትምህርት ግብዓቶችንም ጭምር በመለገስ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ፤ ተቋማቸው የትምህርት ዘርፍን በመደገፍና የተሻለ ትውልድ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ብለዋል።

በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን የትምህርት ተቋማት መልሶ በማቋቋም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ለማስቻል የድርሻውን ይወጣል ሲሉ አረጋግጠዋል።  

በዚህም በ”9222″ የአጭር የጽሁፍ መልዕክት ወይም በቴሌ-ብር የመለያ ቁጥር በመላክ ድጋፋቸውን ማድረግ እንዲችሉ የገቢ ማሰባሰቢያ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ ሁሉም አቅሙ በፈቀደ ከአንድ ብር ጀምሮ ድጋፉን በማድረግ ትውልድን በትምህርት ለማነጽ እና ለመቅረጽ የሚደረገውን ጥረት መደገፍ እንደሚገባው ገልጸዋል።  

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተከፈተው 1000448700945 አካውንትም ድጋፍ ማድረግ እንደሚቻል ተገልጿል።

በውጭ አገራት የሚኖሩ ድጋፍ ሰጪዎች ደግሞ በቴሌብር ዓለም አቀፍ ሃዋላ ወደ 993161616 በመላክ ድጋፍ ማድረግ የሚችሉበትን አገልግሎት መቅረቡ ተጠቁሟል። 

በሌላ በኩል በአይነት የትምህርት ግብቶችን ድጋፍ ለማድረግ የሚፈልጉ ሁሉ በትምህርት ሚኒስቴር ዋናው መስሪያ ቤት በመገኘት ድጋፍ ማድረግ ይችላሉ ተብሏል።