ፍርድ ቤቱ በአማራ ክልል አመራሮች ግድያ ተጠርጥረው ክስ ከተመሰረተባቸው በ28ቱ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ሰጠ

338

ባህር ዳር፤ የካቲት 3/2014 (ኢዜአ) ሰኔ 15/2011 ዓ.ም በአማራ ክልል አመራሮች ግድያ ተጠርጥረው ክስ በተመሰረተባቸው በእነሻምበል መማር ጌትነት የክስ መዝገብ እንዲከላከሉ ከተባሉ 32 ተከሳሾች መካከል በ28ቱ ላይ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ ሰጠ።
ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎት 7ኛ ተከሳሽ የማነ ታደሰ፣ 8ኛ ተከሳሽ ስለሺ ከበደ፣ 11ኛ ተከሳሽ ኮሎኔል ፈንታሁን ሙሃባው እና 12ኛ ተከሳሽ ኮሎኔል ሞገስ ዘገዬም በነፃ እንዲሰናበቱ ውሳኔ ሰጥቷል።

በ28 ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ  የሰጠው  እንዲከላከሉ በተባሉበት ወንጀል የዐቃቤ ህግን ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻላቸው እንደሆነም አመልክቷል።

ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት በህብረትና በማደም ህገ መንግስትና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በመናድ አደጋ ላይ ለመጣልና የክልሉን ስልጣን ባልተገባ መልኩ ለመቆጣጠር በማሰብ የተሳተፉ መሆናቸውን ፍርድ ቤቱ በሰጠው የጥፋተኝነት ውሳኔ ላይ ገልጿል።

በተከሳሾቹ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ የተሰጠውም ተከሳሾቹ የአማራ ክልል አመራሮች የነበሩትን ዶክተር አምባቸው መኮንን፣ አቶ እዘዝ ዋሴን፣ አቶ ምግባሩ ከበደና ሌሎች የልዩ ጥበቃ አባላት በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉና እንዲቆስሉ በማድረጋቸው እንደሆነም አብራርቷል።

ዐቃቤ ህግ ያቀረባቸው የሰው ምስክሮች፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት የተገኙ ማስረጃዎችና የቀረቡ ልዩ ልዩ ሰነዶች ተከሳሾቹ በወንጀሉ የተሳተፉ ስለመሆናቸው በመረጋገጡ ፍርድ ቤቱ ዛሬ የጥፋተኝነት ውሳኔ  መስጠቱን አስታውቋል።  

በነፃ እንዲሰናበቱ የተወሰነላቸው አራቱ ተከሳሾች እንዲለቀቁም ችሎቱ ለባህር ዳር ማረሚያ ቤት ትዕዛዝ ሰጥቷል።

የጥፋተኝነት ውሳኔ የተሰጣቸው 28 ተከሳሾች የፍርድ ማቅለያቸውን ይዘው እንዲቀርቡ ለየካቲት 7/ 2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት የዕለቱ ችሎት ተጠናቋል።