ኦሮሚያ ለአማራ ክልል 100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

85

ባህር ዳር የካቲት 3/2014 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ክልል በአሸባሪው የህወሃት ቡድን በአማራ ክልል የደረሰውን ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት መልሶ ለማቋቋም የ100 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ።

የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ  ድጋፉን ለአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ለዶክተር ይልቃል ከፍአለ አስረክበዋል ።

ርእሰ መሰተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በወቅቱ እንዳሉት በአማራና አፋር የደረሰው ውድመትና የተከፈለው መስዋትነት የታሪክ ጠባሳ አሳድሯል።

አሸባሪ ቡድኑን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት መመለስ መቻሉ የኢትዮጵያውያን ሃያልነትን ያረጋገጠ መሆኑን ገልፀዋል።

በአማራ ክልል የደረሰውን ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት ለመመለስ ለሚደረገው ጥረት የኦሮሚያ ክልል የ100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

"በቀጣይም ችግሩ እስኪቀረፍና የወደመውን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት የጀመርነውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን" ሲሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ  አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፍአለ በበኩላቸው "ጠላቶቻችንን ማሸነፍ የምንችለው አንድነታችን በማጠናከር ነው" ብለዋል።

"የኦሮሚያ ክልል በአሸባሪው ሸኔና በቦረናና ጉጅ ዞኖች በተከሰተው ድርቅ ችግር ውስጥ ሆኖ ያደረገው ድጋፍ የአብሮነታችን እና የመተሳሰባችን መገለጫ ማሳያ ነው" ሲሉም ተናግረዋል ።

"የተደረገው ድጋፍ ከደረሰብን ጉዳት ፈጥነን እንድንወጣ ያግዘናል " ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም