የወጪ ንግድን ለማሳደግ የመንግስትና የግል ባለሃብቱን ተቀራርቦና ተቀናጅቶ መስራት ይጠይቃል

97

የካቲት 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) የወጪ ንግድን ለማሳደግ የመንግስትና የግል ባለሃብቱ ተቀራርቦና ተቀናጅቶ መስራት በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን በንግድ ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዛሬ በወጭ ንግድ ዘርፍ ከተሰማሩ ባለሃብቶችንና ማኅበራት ጋር ውይይት አካሂዷል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች የወጪ ንግዱን ለማሳደግና አገሪቷ ከዘርፉ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ መንግሥት ለዘርፉ ተዋናዮች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆንና ምርቶችን ለማስተዋወቅ መንግሥት ብድርን ጨምሮ የተለያዩ የፋይናንሰ ድጋፎችን ሊያጠናክር እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ፀሃፊ አቶ ሺበሺ ቤተ-ማሪያም በተወሰኑ ምርቶች ላይ ብቻ የተንጠለጠለውን የአገሪቷ  የወጪ ንግድ ማሻሻል ይጠበቃል ብለዋል።

በሌላ በኩል ለወጪ ንግድ የሚቀርቡ አብዛኞቹ የግብርና ምርቶች በመሆናቸው ለተለያዩ ችግሮች የሚጋለጡበት አጋጣሚ መኖሩን ጠቁመዋል።

ይሁንና የፋይናንስና መሰል ግብዓት ችግሮች ቢኖሩም የተለያዩ መፍትሄዎችም እየተሰጡ እንደሚገኙ የጠቀሱት አቶ ሺበሺ፤ ለአብነትም የፖሊሲ ቀረጻን አንስተዋል፡፡

የወጪ ንግዱን እሴት ጨምሮ በመላክ ገቢውንም ጥራቱንም ማስጠበቅ ይቻላል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ የወጭ ንግዱ በየዓመቱ እድገት እያሳየ መሆኑን ጠቅሰው፤ ባለፈው ዓመት ከ3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።

የንግድ ሥርዓቱ የተዛባባቸው አገራት የውጭ ምርቶች ወደ አገራቸው እንዳይገቡ በከለከሉበት አስቸጋሪ ወቅት ይህን ውጤት ማስመዝገብ መቻሉ የሚያበረታ መሆኑን ጠቁመዋል።  

መንግሥት በዘርፉ የሚታዩትን ማነቆዎች ለመፍታት እየወሰደ ያለውን እርምጃ ያደነቁት የውይይቱ ታዳሚዎች አሁንም የሚታዩ ክፍተቶችን ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም