የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች በጎርፍ የተጎዱ አከባቢዎች እንዲያገግሙ አስችሏል

121

ጂንካ ፤የካቲት 1/2014 (ኢዜአ) ባለፉት ዓመታት ተፋሰሶችን መሰረት በማደረግ የተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች በጎርፍ ተቦርቡረው የተጎዱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ ማስቻሉን የደቡብ ኦሞ ዞን ግብርና መምሪያ ገለጸ ።
በዞኑ 240 ሺህ የሚሆኑ አርሶ አደሮችን ያሳተፈ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ንቅናቄ እየተከወነ ነው ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ባንኬ ሱሜ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በዞኑ በጎርፍ አደጋ ምክንያት የተራቆቱ አካባቢዎችን ለመታደግ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑት የማልማት ስራዎች መልሰው ማገገም ችለዋል።

ባለፈው ዓመት በ287 ንዑስ ተፋሰሶች ከተተከሉ 26 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን መካከል 85 በመቶ መጽደቁን  በዳሰሳ ጥናት መረጋገጡን ጠቅሰዋል።

ውሃን የሚያቅቡ የተለያዩ እርከኖችና የችግኝ ተከላ ስራዎች የመሬት መሸርሸርን ከመከላከል ባሻገር ውሃን እንድያሰርግ በማድረጉ የደረቁ ምንጮች  እንዲመነጩ ማስቻሉንም አመላክተዋል ።

በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራዎች  ካገገሙ አካባቢዎች መካከል  የባዘት ተፋሰስ ተጠቃሽ መሆኑንም አስረድተዋል።

የጂንካ ከተማ አስተዳደር ግብርና ጽህፈት ቤት የባዘት ቀበሌ አስተባባሪ አቶ አዳሙ በዛብህ፤ አከባቢው በከፍተኛ ሁኔታ በጎርፍ የተጠቃ መሆኑን ጠቅሰው ጎርፉ በጂንካ ከተማ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት ያደርስ እንደነበር ተናግረዋል ።

ተፋሰስን መሰረት በማድረግ በተከናወኑት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሰራዎች የጎርፍ አደጋን በመከላከል የተራቆቱ አከባቢዎችን እንዲያገግሙና ለነዋሪው ጥቅም ወደመስጠት  መሸጋገራቸውን ገልጸዋል።

በጂንካ ከተማ አስተዳደር የአልጋ ቀበሌ በተመረጠ ተፋሰስ  ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ላይ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት አርሶ አደር ገርታ ገማይ እንዳሉት፤ አካባቢው ተዳፋት በመሆኑ በየጊዜው የአፈር መሸርሸር ስለሚከሰት በዘሩት ሰብል ላይ ጉዳት ይደርስ ነበር።

በሌሎች ቀበሌዎች በተሰራው የተፋሰስ ልማት የተሻለ ውጤት መገኘቱንና የተጎዱ አከባቢዎች እያገገሙ ማየታቸውን  ገልጸው፤ በዘንድሮው ስራ ላይ በሙሉ ፍላጎት  እየተሳተፍኩ ነው ብለዋል ።

የጎርፍ  አደጋውን  ለመከላከል የተፋሰስ ስራ ጠቀሜታ እንዳለው ግንዛቤ በመውሰድ በልማቱ እየተሳተፉ  መሆናቸውን የተናገሩት የቀበሌው ነዋሪ ወይዘሮ አልቆ በዛብህ ናቸው ።

በተፋሰስ ልማቱ በሚለሙ ስፍራዎች ላይ ፍራፍሬዎችን እና አትክልቶችን በማልማት ተጠቃሚ ለመሆን እየሰሩ እንደሚገኙ ተናገረዋል።

ዘንድሮም በዞኑ 26 ሺህ ሄክታር መሬት ያካለለ 308 ንዑስ ተፋሰሶችን ለማልማት የንቅናቄ  ስራ እየተካሄደ ነው።

ስራው በሚሸፈኑ ቦታዎች ላይ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን 40  ሚሊዮን የደንና  የፍራፍሬ ችግኞችን  ለማልማት መታቀዱን  ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም