በኢትዮጵያ የማንፋክቸሪንግ ዘርፍ ተስፋ ሰጪ ስኬቶችን ማስመዝገብ ጀምሯል

61

ሀዋሳ፣  ጥር 30/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ኢኮኖሚውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየተተገበረ ያለው የማንፋክቸሪንግ ዘርፍ ተስፋ ሰጪ ስኬቶችን ማስመዝገብ መጀመሩን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።

በናይጄሪያ ግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስትር ዶክተር መሐመድ ማህሙድ አቡበከር የተመራ የልዑካን  ቡድን የቡልቡላ ኢንዱስትሪ ፓርክን ዛሬ ተዘዋውሮ ጎብኝቷል።

አቶ መላኩ የማንፋክቸሪንግ እድገት መፋጠን ከሌሎች ዘርፎች  በተሻለ ኢኮኖሚውን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል ብለዋል።

ዘርፉ ከኢኮኖሚው እድገት እና ስራ እድል ፈጠራ፤ በተለይም ከግብርናና አገልግሎት ጋር ግንኙነት ያለውና  ለቴክኖሎጂ እድገት  ማረጋገጫ እንደሆነም አስረድተዋል።

መንግስት ገበያ ተኮር ግብርናን በመገንባትና የግብርና ማቀነባበሪያ ዘርፉን በማጠናከር እሴት የተጨመረባቸው ምርቶችን ለዓለም ገበያ በማቅረብ የውጭ  ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ  አቅዶ ሲተግብር መቆየቱን ጠቁመዋል።

የግብርና-ኢንዱስትሪ ዘርፍን ማጎልበት  የዘርፉን ገቢ አመንጪነት ለማሳደግ እና አዲስ ዘላቂ የስራ ዕድሎችን ለመፍጠር  የሚያበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።

በተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱሰተሪያል  ፓርክ መጀመሪያ ላይ  17 የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ልማት ኮሪደሮችን በመላ ሀገሪቱ መለየታቸውን አብራርተዋል።

ከተለዩት ኢንዱስትሪ ልማት ኮሪደሮች ለሙከራ አራት ቦታዎች ቅድሚያ እንደተሰጣቸው ሚኒስትሩ ለልዑካን  ቡደን ገለጻ አድርገዋል።

የግብርና ምርቶችን የማምረት አቅም፣  የአስፈላጊ የሆኑ የመሠረተ ልማት አውታሮች አቅርቦት፣  ባለሀብቶችን ማሳመን እና  በግብርና ማቀነባበሪያ ልምድ ማመቻቸት የሚሉት የሙከራ ቦታዎችን ለመምረጥ የተጠቀሙባቸው መስፈርቶች እንደነበሩም ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት በዘርፉ ተስፋ ሰጪ ስኬቶችን ማስመዝገብ መጀመሩን ገልጸዋል።

ይህም በተቀናጀ የግብርና ውጤቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱሰተሪያል ፓርኮች  ዋና ዋና መሰረተ ልማቶችን በማጠናቀቅ በምግብ ማቀነባበሪያ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ዝግጁ በማድረግ ረገድ የተገኘው ውጤት እንደሆነ አመላክተዋል።

የሚፈለገውን ካሳ በመክፈል 1ሺህ 296 ሄክታር መሬት ነፃ በማድረግ  ከተገነቡት  የተቀናጀ የግብርና ውጤቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል  ፓርኮች ሶስቱ  ስራ መጀመራቸውን ጠቁመዋል።

በምግብ ማቀነባበሪያዎች የሚፈለጉትን የመሰረተ ልማት አውታሮች በመጠቀም ለዘርፉ ኢንቨስትመንት መጨመር ምቹ ሁኔታን መፈጠሩንም አብራርተዋል።

ፓርኮቹ ከ945 ሺህ  በላይ ለሚሆኑ አነስተኛ አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር ይፈጥራሉ፤ይህም የግብርናውን ዘርፍ ወደ ንግድ ለማሸጋገር ተስፋ ሰጪ  ነው ብለዋል።

በፓርኮቹ ውስጥ  ከ24 በላይ የሀገር ውስጥ ኢንተርፕራይዞች መገንባታቸውን ተናግረዋል።

በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኘ ፓርኮች ከ25 ሺህ 500 ለሚበልጡ ሰዎች ጊዜያዊ የስራ እድል እና  የኦፕሬሽን ኢንተርፕራይዞች ቋሚ የስራ እድል መፈጠሩን ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

የልኡካን በቡድኑ ከናይጄሪያ ሰባት የከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ  ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን ያካተተ መሆኑ ታውቋል።

የቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የስራ እንቅስቃሴ መመልከትና የልምድ ልውውጥ ማድረግ እንዲሁም በሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ የተቀናጀ የግብርና ውጤቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮችና ላይ የናይጀሪያ ባለሀብቶች እንዲሰማሩ ማመቻቸት  የጉብኝቱ ዓላማ ነው።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም