በማህበራዊ ድረ-ገጾች የሚሰራጩ አንዳንድ መልዕክቶች የግጭትና የጥፋት ምክንያት እየሆኑ ነው-ምሁራን

82
አዲስ አበባ  ነሀሴ 25/2010  ኢትዮጵያን በተመለከተ በማህበራዊ ድረ-ገጾች የሚሰራጩ አንዳንድ መልዕክቶች የዜጎችን በአንድነት የመኖር እሴት በማናጋት የአገርና ህዝብን ሰላም ለአደጋ እየዳረጉ ናቸው ሲሉ ምሁራን ገለጹ። በመሆኑም ህብረተሰቡ በማህበራዊ ድረ-ገጾች የሚሰራጩ ሀሰተኛና ሰላምን የሚያደፈርሱ መረጃዎችን በጥንቃቄ ማየትና መረዳት አለበት ብለዋል። በተለይም ወጣቶች መረጃዎችን እንዳለቀለት እውነት ከመቀበለ በመቆጠብ የመመርመር ባህልን ሊያዳብሩ ይገባዋል ነው ያሉት። ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ በማህበራዊ ድረ-ገጾች የሚለቀቁ የጥላቻ፣ የዘረኝነትና መሰል ይዘት ያላቸው ወሬዎች በአሳሳቢ ደረጃ በመስፋፋት ላይ ናቸው። በተለይ ወጣቱ እውነተኝነታቸው ባልተረጋገጡ የማህበራዊ ሚዲያ ወሬዎች ምክንያት ስሜታዊ በመሆን አላስፈላጊ የጥፋት ተግባር ላይ ሲሳተፍ ማስተዋል የተለመደ ክስተት እየሆነ መጥቷል። በመሆኑም ወላጆች፣ ትምህርት ቤቶች፣ መገናኛ ብዙሃንና የእምነት ተቋማት በእነዚሀ ድረ-ገጾች የሚሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎችን በተለይም ወጣቱን ማስተማርና መምከር እንደሚጠበቅባቸው ምሁራኑ አሳስበዋል። እንደ ፌስቡክና ዩቱዩብን በመሳሰሉት የማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጨው እውነትነት የሌለውና ለግጭት የሚያነሳሳ መልዕክት በዚሁ ከቀጠለ በኢትዮጵያ የሚታየው ተስፋ ሰጪ የለውጥ ሂደት እንቅፋት መሆኑ አይቀርም ሲሉም ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን አስጠንቅቀዋል። ተግባሩ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የምትታወቅበትን የመቻቻልና የመከባበር ባህል የሚያጠፋና በዜጎች መካከል ጥላቻና ግጭት የሚፈጥር በመሆኑ በተለይ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት እውነተኛ መረጃዎችን ለህዝብ በማድረስ በኩል ሚናቸው ከፍተኛ ሊሆን ይገባል ብለዋል። ዶክተር ወልደአብ ተሾመ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቱ የሶሺዮሎጂ መምህር እንደተናገሩት ሶሻል ሚዲያ  የሚያወጣቸው አስቸጋሪ የሆኑ ወጣቱ በስሜት እንዲንቀሳቀስ የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች ይወጣሉ እና የሚዲያ ተቋማት ደግሞ ይሄንን እየተከታተሉ ደግሞ እውነቱን መግለጽ፣ ማሳወቅ፣ ማስተማር አለባቸው የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎችም የትምህርት ተቋማት የውይይት መድረኮችን በመክፈት፣ ምሁራንም በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ለአገር የሚበጀውን መንገድ የመጠቆም ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል። "በአገር ጉዳይ ላይ ችግር ከደረሰ በኋላ ችግሩን ለማጥፋት መረባረብ ዋጋ አይኖረውም" የሚሉት ምሁሩ "በመንግስት በኩል ችግሩ ሊፈጠር ይችላል ብሎ ቀድሞ በማሰብ የጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ፣ ችግር በሚፈጥሩት ላይ ደግሞ አስተማሪ ቅጣት ሊኖር ይገባል፤" ሲሉ ተናግረዋል። የታሪክ ተመራማሪና ጸሃፊ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩሉ በማህበራዊ ድረ-ገጾች የሚሰራጩ እውነታቸው ያልተረጋገጡ መልዕክቶች የሰውን ስሜት እየጎዱና በተለይ ወጣቱ በአገሩ ላይ አላስፈላጊ ነገሮችን እንዲያደርግ መንገድ በመክፈት ላይ ነው ይላል። "በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚደረጉ እኩይ ተግባራት ፈጽሞ ኢትዮጵያዊነትን የማይገልጹ ናቸው" ያለው ዲያቆን ዳንኤል በአገር ጉዳይ ላይ በሚከሰት ማንኛውም ተግባር በተለይ ወጣቱ ነቅቶ መጠበቅ እንደሚገባው አስገንዝቧል። ህብረተሰቡ በማህበራዊ ድረ-ገጾች የሚሰራጩ ሀሰተኛና ሰላምን የሚያደፈርሱ መረጃዎችን በጥንቃቄ ማየትና መረዳት አለበት ነው ያሉት ምሁራኑ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም