የኢትዮጰያያና የኤርትራ መሪዎች የሰላም ስምምነት ተከትሎ የሁለቱ ሃገራት አጎራባች ነዋሪዎች አዲሱን ዓመት በጋራ ሊያከብሩ ነው

91
ሽሬ እንዳስላሴ ነሀሴ 25/2010 የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የኤርትራው ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ያደረጉትን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የሁለቱ ሃገራት አጎራባች ነዋሪዎች የዘመን መለወጫ በዓልን በጋራ ለማክበር እየተዘጋጁ ነው፡፡ በሁለቱ ሀገራት አጎራባች ድንበር አካባቢ የሚኖሩት  ኢትዮጵያዊያን  ለኢዜአ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን በደምና በታሪክ የተሳሰሩት ህዝቦች ናቸው፡፡ የተፈጠረልንን የሰላም እድል ተጠቅመው አዲሱን የዘመን መለወጫ በዓል አብራው በጋራ ሆነው  በደስታ ፣ በፍቅርና መተሳሰብ ለማክበር ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን በሁለቱም ሀገራት ድንበር አከባቢ ከሚገኙት  ኢትዮጵያዊያን መካከል የአዲ ፀፀር ቀበሌ ነዋሪ አቶ መብራህቶም ግርማይ በሰጡት አስተያየት  ቀደም ባሉት ዓመታት የዘመን መለወጫ በዓልን የሚያከብሩን በስጋት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ሁለቱም መንግስታት ያደረጉት የሰላም ስምምነት ተከትሎ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በጀመሩበት ወቅት የሚከናወነው ቀጣዩ  አዲሱ  የዘመን መለወጫ በዓል በፍቅርና በመተሳሰብ ለማክበር እድል በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ሌላው የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ቄስ መሓሪ ይርጋ በበኩላቸው ከ20 ዓመታት በኋላ ያለ ስጋት የሚቀበሉት ቀጣዩ  አዲስ ዓመት ለሁለቱም ወንድማማች ህዝቦች መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ካደረጉት የሰላም ስምምነት በኋላ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መጀመሩን ተከትሎ መጪው አዲስ ዓመት ከኤርትራዊያን ወንድሞቻቸው ጋር በፍቅር ለማክበር እየተዘጋጁ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በታህታይ አዲያቦ ወረዳ የአዲ አሰር ቀበሌ አርሶ አደር በላይ ሓድጉ ናቸው፡፡ የገምሃሎ ቀበሌ  ነዋሪው አቶ ወልደሩፋኤል ተክላይ በበኩላቸው መጪው አዲስ ዓመት በሁለቱም ሀገራት  መካከል የተፈጠረውን ሰላም ዘላቂ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡ የአካባቢ የአስተዳደር አካላትም የህዝቡን ፍላጎትና ምኞት ለማሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም