በአፍሪካ የወባ ወረርሽኝ የሚያስከትለውን የሞት ምጣኔ ለመቀነስ የተያዘውን እቅድ ኢትዮጵያን ጨምሮ 15 አገራት አሳክተዋል

80

ጥር 29/2014/ኢዜአ/ በአፍሪካ በ2020 የወባ ወረርሽኝ የሚያስከትለውን የሞት ምጣኔ ለመቀነስ የተያዘውን እቅድ ኢትዮጵያን ጨምሮ 15 አገራት ማሳካታቸውን የአፍሪካ መሪዎች የወባ በሽታ መከላከል ሊቀመንበር የኬኒያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ተናገሩ።
የወባ በሽታ የአፍሪካ ስጋት እንዳይሆን አገራት የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው ሊያስቀጥሉ ይገባል ብለዋል።

በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ የአፍሪካ መሪዎች የወባ በሽታ መከላከል ሊቀመንበር የኬኒያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፤ በአፍሪካ የወባ በሽታን ተጽዕኖና እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን በተመለከተ ሪፖርት አቅርበዋል።

እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለፃ እ.አ.አ በ2020 በአፍሪካ የወባ ወረርሽኝ የሚከሰተውን የሞት ምጣኔ 40 በመቶ ለመቀነስ የታቀደ ቢሆንም ማሳካት የቻሉት አገሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ 15 ብቻ ናቸው።

በተለይ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት የወባ በሽታን ለመከላከል የተጀመረው ሂደት ትኩረት እንዳያገኝ እንቅፋት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሆኖም 23 የአፍሪካ አገራት የወባ ወረርሽኝን ለመግታት ሁሉን አቀፍ ንቅናቄ ለማድረግ የሀብት ማሰባሰብ  ስራ መጀመሩን አንስተዋል።

በተጨማሪም 24 የአፍሪካ አገራት የወባ ወረርሽኝን ለመግታት ብሄራዊ የወባ መከላከያ ምክር ቤት ማቋቋማቸውን ገልጸዋል።

እኤአ በ2021 የዓለም ጤና ድርጅት ከ5 አመት በታች ላሉ ህጻናት የወባ በሽታ ክትባት የጀመረ መሆኑን በማንሳት ይህም የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል የተጀመረውን ጥረት የሚደግፍ ነው ብለዋል።

በርካታ አገራት የአፍሪካ የመድሃኒት ኤጀንሲ ስምምነትን መፈረማቸውም የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል መልካም ተስፋ የሰነቀ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የወባ ወረርሽኝ የአፍሪካ ስጋት እንዳይሆን አገራት የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው እንዲያስቀጥሉ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የወባ በሽታን ለመከላከል መንግስታት ከሚያደርጉት ጥረት ጎን ለጎን የሚዲያ አካላትም በጉዳዩ ለይ ትኩረት ሰጥተው በመስራት ግንዛቤ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

እ.አ.አ ከ2000 ጀምሮ አስካሁን ድረስ በአፍሪካ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሰዎች በወባ ወረርሽኝ ለህልፈት መዳረጋቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም