የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይት አድርጓል

58

ጥር 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) 35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በዝግ ባደረገው ስብሰባ በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይት ማድረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ፡፡

ጉባኤው ከትናንት ረፋድ ጀምሮ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን፤ በከሰዓት በኋላ መርሃ- ግብሩም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በዝግ መክሯል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት መግለጫ፤ ጉባኤው በአህጉሪቷ የሰላምና ደህንነት ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይት ማድረጉን ተናግረዋል።

በአፍሪካ እየተበራከተ የመጣውን ሕገ-መንግስታዊ ያልሆነ የመንግስት ግልበጣ አሳሳቢነት ላይ መምከሩን የጠቀሱት አምባሳደር ዲና፤ የኬኒያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ ጉዳዩን በሚመለከት ሰፊ ማብራሪያ ማቅረባቸውንና በርካታ መሪዎች ደግሞ የጉዳዩ አሳሳቢነት ላይ ያላቸውን ሃሳብ መግለጻቸውን ተናግረዋል፡፡

ሌላው በዝግ ውይይት የተደረገበት ጉዳይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመከላከል ረገድ የተደረጉ ጥረቶችና የተገኙ ውጤቶች ላይ ነው፡፡

በተለይ የኮቪድ-19 ክትባትን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል የጤና ስርዓት መዘርጋትን በሚመለከትም መሪዎቹ ውይይት ማድረጋቸውን ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ ጉባኤው የአፍሪካ ልማት ባንክ የአህጉሪቷን ውህደት ለማፋጠን በሚያስፈልግ ፈንድ ዙሪያ ባቀረበው ሪፖርት ላይ ውይይት አድርጓል ነው ያሉት፡፡

ጉባኤው በዛሬ እለት ቀጥሎ የሚካሄድ ሲሆን፤ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም