ኢትዮጵያ ሰላም ነች

473

ቀደሰ ተክሌ - ኢዜአ

በጠንካራ ዓለት ላይ የተመሠረተ ቤት ተምሳሌት ነች ኢትዮጵያ። በጠንካራ አለት ላይ መመስርቷ ከግራም ከቀኝም፣ ከሀገር ውስጥም ከውጭም በሚነፍስ የጥፋት ንፋስ፣ የመከፋፈል ማዕበል፣ የመፍረስ ወጀብና ጎርፍ እንድትፈርስ አላደረጋትም። ህዝቦቿ በጠንካራ ስብዕናና ሞራል የተሰናሰሉ፤ማንም ሊፈታው በማይችል የአብሮነት ገመድ የተጋመዱ፣ የኃያላኑን ሴራ በጥበብ ማሸነፍ የሚችሉ፣ ለዘመናት እያዳበሩ የመጧቸውን በጎ የሆኑ ማህበራዊና ባህላዊ እሴቶች ጠብቀው የኖሩ፣ ለዛሬው ትውልድ ያስተላለፉ፣ ወደፊትም እንዲተላለፍ አበክረው የሚሰሩ፤ ለሰላም ትልቅ ቦታ ያላቸው እንግዳ አክባሪነታቸው የተመሰከረላቸው ናቸው።

ከስንዴ መካከል እንክርዳድ፣ ከፍሬ መካከል ገለባ እንማይታጣው ሁሉ ከሰላም ወዳዱና  ለሀገሩ ክብር ሟች ከሆነው ኢትዮጵያዊ መካከል ራስ ወዳድ የሆኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ኢትዮጵያንና ህዘቦቿን ሰላም ነስተዋል። የንጹሃንን ህይወት ቀጥፈዋል፣ አካል አጉድለዋል፣ ሀብትና ንብረት አውድመዋል።ያለ የሌለ አቅማቸውን አሟጠው በመጠቀም የህዝቦችን አንድነት ለመሸርሸር ኢትዮጵን ለማፍረስና የጦርነት ቀጠና ለማድረግ ብዙ ጥረዋል።

በመንግስትና በሕዝቡ የተቀናጀ ትብብር አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔን ጨምሮ የኢትዮጵያና የህዝቦቿ የጥፋት ድግስ ደጋሾቹ ሀሳባቸው መክኖ፣ ህልማቸው ቅዠት ሆኖ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ሰላማቸውን እያረጋገጡ ጉዟቸውን  ወደ ፊት ቀጥለዋል።

ጠላቶቿ እንደ አሸን የፈሉት ኢትዮጵያ ሰላም እንዳልሆነች አድርገው የሐሰተኛ መረጃ ዘመቻ ቢከፍቱም፣ ዜጎቻቸውን ከኢትዮጵያ እንዲወጡና ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ቢጎተጉቱና  ዓለም ፊቱን እንዲያዞር የሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ሌት ተቀን ቢደክሙና የአየር በረራም እስከመከልከል ያላቸውን ፍላጎት በገሃድ ቢያሳዩም  ምኞታቸው ከንቶ ሆኖ ቀርቷል።

''እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል'' እንዲሉ ኢትዮጵያ የያዘችው እውነት በተለያዩ ኹነቶች ለጠላቶቿ ግልጥ ብሎ ታይቷል። ጆሯቸውን ጭው የሚያደርጉ፣ ለእይታ የሚያስደነግጡ የኢትዮጵያን እንደ ሀገር መቀጠል የሚያረጋግጡ፣ የህዝቡን አንደነት በጉልህ የሚያሳዩ የልማት ስራዎች፣  የኢትዮጵያን አትንኩ ህዝባዊ ትይንቶች፣ በችግር ውስጥ ሆኖም እድገትና ልማት እንዳልቆመ የሚያሳዩ የልማት ስራዎች፣ የህዝብ የአደባባይ በዓላት፣ የደስታና የድል ዜናዎችን ደጋግመው  ከኢትዮጵያ ሰምተዋል።

ኢትዮጵያ ሰላም ነች፣ ትናትም ሰላም፣ ዛሬም ሰላም፤ ነገም ሰላም፤የውስጥ ችግሮቿን በዘላቂነት በመፍታት ይበልጥ አንድነቷን እና ሰላሟን  ለማረጋገጥ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ሀገራዊ የጋራ ምክክር መድረክ ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅተ ስራዎች እየተሰሩ ነው።

አሸባሪው ህወሓት፣ ተላላኪዎቹና ላኪዎቹ ህብረት ፈጥረው በከፈቱት ጦርነት በህልውና ዘመቻ ላይ የቆየችው ሀገር ዛሬ ላይ ዘመቻውን በድል በማጠናቀቅ ሰላም መሆኗን በተለያዩ ኹነቶች እያረጋገጠች ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አንድ ሚሊዮን ለሚሆኑ የዳያስፖራ አባላት ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ በተለያዩ የዓለም ሀገራት ኑሯቸውን ያደረጉ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ  ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው በመግባት ኢትዮጵያ ሰላም መሆኗን አረጋግጠዋል።

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል መምህር አጥናፉ ምትኩ በተለይ የአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራዎች የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለው ወደ ሀገር ውስጥ መግባት የአንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራትና የመገናኛ ብዙሃንን የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ያመከነ መሆኑን ተናግረዋል። ዳያስፖራዎች ከዓለም ሀገራት በተለይም ኢትዮጵያ ሰላም አይደለችም እያሉ በየቀኑ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ከሚያሰራጩ ሀገራት ጭምር  የመጡ መሆናቸው  ደግሞ የተለየ ትርጉም የሚያሰጥ ነው። ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡም በአዲስ አበባ ብቻ ሳይወሰኑ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች መዘዋወራቸው ኢትዮጵያ ሰላማዊት ሀገር መሆኗን ይበልጥ አረጋግጧል ብለዋል።

ከጦርነቱ ማግስት ኢትዮጵያ ሰላም እንዳልሆነች የውጭ ሚዲያዎች በተቀናጀ መልኩ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ሲነዙ ጦርነቱ በተካሄደበት የሰሜኑ የሀገራችን ክፍል አንዱ በሆነው ላልይበላ እንኳ የልደት በዓል ኃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ በርካታ ቱሪስቶች በተገኙበት  በድምቀት ተከብሯል። አዲስ አበባ ሰላም አይደለችም ላሉት በላልይበላ የተከበረው በዓል እጃቸውን በአፋቸው የሚያስጭንና ያስደነገጣቸው ክስተት መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም።

በገና ማግስት የኢትዮጵያ ልዩ መገለጫ የሆነውና በዩኔስኮ ተመዝግቦ የዓለም ቅርስ የሆነው የጥምቀት በዓል በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በታላቅ ድምቀት ተከብሯል። ብዙ ሰዎች የሚታደሙበት ይህ የአደባባይ በዓል የአፍሪካ ህብረት፣ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ በሆነችው  አዲስ አበባም በታላቅ ድምቀት ተከበረ። አዲስ አበባ ሰላም አይደለችም እያሉ የሀሰት መረጃ ለሚያናፍሱ አካላት ይህ ክስተት ማስደነቁ ሳያንስ  የጥምቀት በዓል በጎንደር በልዩ ሁኔታ ተከብሯል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሀገር ውስጥ በረራ በአንድ ቀን ውስጥ እጅግ በርካታ ምልልሶችን በማድረግ አዲስ ታሪክ አስመዘገብ። ከፍተኛ ቁጥር ያለው  የቱሪስት ፍሰት የታየበት ይህ ደማቅ በዓል በጎንደር ሲከበር ኢትዮጵያ ደምቃና ከፍ ብላ ታይታለች፤ ይህ ሁሉ እውነት ያለው በኢትዮጵያ ነው፤ ያ ሁሉ የውሸት ዜና መነሻ ደግሞ ከመሰረተ-ቢስ ጥላቻ ውጭ ሌላ ምንጭ የለውም።

''አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም'' እንዲሉ አበው ይህን ሁሉ ክስተት በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ቢመለከቱም ኢትዮጵያ ሰላም ነች ማንም ገብቶ መውጣት ይችላል ሊሉ ግን አልወደዱም። አሁንም ወደ ኢትዮጵያ አትግቡ ሰላም አይደለችም ሲሉ ይወተውታሉ። እንደ ምሁሩ ገለጻ የዚህ ሁሌ ሴራ ዓላማ  35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ እንዳይካሄድ በመሻት ነው።

እንደ ክፉዎች ሴራ ሳይሆን በኢትዮጵያ መንግሥትና በወንድምና እህት የአፍሪካ መሪዎች ጥረት ነገ የሚጀመረው  የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በህብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰኑ የኢትዮጵያን ሰላም መሆን ይብልጥ አረጋግጧል። ኢትዮጵያ ችግር በገጠማት ጊዜ ሁሉ አፍሪካውያን ከጎኗ በመሆን አጋርነታቸውን በተግባር አሳይተዋል።ኢትዮጵያም አፍሪካዊ ወንድማማችነትን በሚያጠናክር መልኩ በህብረቱ መሬዎች ጉባኤ ለመሳተፍ የሚመጡ እንግዶችን እየተቀበለች ነው።

ምሁሩ እንዳሉት አፍሪካውያን ያልተገባ ጫናና ጣልቃ ገብነት በቃ በማለት የራሳቸውን ጉዳይ በራስ የመወሰን መብታቸውን ተጥቅመው ጉባኤው አዲስ አበባ እንዲደረግ መወሰናቸው ሳያገባቸው ገብቶ ማቡካት የሚሹ ሀገራትን አንገት አስደፍቷል።

የአፍሪካውያንን ፍጹም ወንድማማችነትና አንድነት የሚያጠናክር ትልቅ አንድምታ ያለውን ውሳኔ በማስተላለፍ መሪዎቹ አፍሪካውያን ቀና እንዲሉና አንዳንድ የምዕራባዊያን ሀገራት ደግሞ ወደ እውነቱ መለስ እንዲሉ አድርገዋልና ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ክፍል መምህር ሙሉቀን አየለ በበኩላቸው መሪዎቹ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን ለመፍታት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዳንጸባረቁ ገልጸዋል። የዚህ እሳቤ አንዷ አካልና ተሟጋች የሆነች ሀገር ኢትዮጵያ ጎን በበቃ ንቅናቄ ተሰልፈው በራስ የመወሰን መርህን መተግባር መጀመራቸው የሚበረታታ መሆኑን አክለዋል።

የአፍሪካ መሪዎች ለኢትዮጵያውያን ብዙ መልዕክቶች ያሉትን ውሳኔ እንደወሰኑ ጠቅሰው እርስ በርሳችን እንድንባላ አጀንዳ ፈጥረው የሚሰጡ አካላትን በቃ ልንል ይገባል። የመሪዎቹ ጉባኤ  በኮሮና ምክንያት በአካል ከመካሄድ ከተቋረጠበት ሁለት ዓመት በኋላ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ኢትዮጵያ ተሰናድታ እንግዶችን እየተቀበለች ነው።

የአፍሪካ ህብረት 35ኛው መደበኛ የመሪዎች ጉባኤ ''የአፍሪካ አህጉርን የስርዓተ ምግብ አቅም መገንባት፣ የሰው ሀበት ልማት፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማትን ያፋጥናል'' በሚል መሪ ሀሳብ ነገ እና ከነገ በስትያ  በህብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

ታዲያ ከዚህ ሌላ ሰላም እንዴት ያለ ነው? "ከባለቤቱ በላይ ያወቀ ቡዳ ነው" እንዲሉ የኛን ሰላም የምናውቀው እኛ ኢትዮጵያውያን - እኛ አፍሪካውያን ብቻ ነን። ኢትዮጵያ ሰላም ነች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም