በአፍሪካ ዘላቂና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማምጣት የእርስ በርስ የንግድ ትስስሩን ማጠናከር ይገባል

ጥር 26/2014/ኢዜአ/ በአፍሪካ ዘላቂና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማምጣት የእርስ በርስ የንግድ ትስስሩን ማጠናከርና ምርቶችን እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደሚገባ የአፍሪካ ህብረት የኢኮኖሚ የልማት፣ ንግድ፣ ኢንዳስትሪና ማዕድን ኮሚሽን ገለጸ።

የሕብረቱ ኮሚሽን የኢኮኖሚ የልማት፣ ንግድ፣ ኢንዳስትሪና ማዕድን ኮሚሽን የዘርፉን አፈጻጸም አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር አልበርት ሙቻንጋ፣ ዘርፉ አሁንም በፈተና ውስጥ ይገኛል ብለዋል።

በተለይም የአፍሪካ የንግድና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ከማደግ ይልቅ አሁን ላይ ማሽቆቅል እየታየበት ይገኛል ነው ያሉት።

አህጉሪቷ ወደ ውጭ የምትልካቸው ምርቶች በአብዛኛው ከጥሬ እቃነት የዘለለና የምርት ሂደታቸው ተጠናቆ እሴት ያልታከለባቸው መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ሁኔታው አፍሪካ ራሷ በጥሬ እቃነት የላከቸውን ምርት ተቀናባብሮ ያለቀለት ምርት ከውጭ እድታስገባ እያደረጋት መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም በአፍሪካ ዘላቂና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማምጣት የእርስ በርስ የንግድ ትስስሩን ማጠናከርና ምርቶችን እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ይገባል ነው ያሉት።

ኮሚሽነሩ አክለውም አብዛኛው የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት ነጻ በወጡ ማግስት የአህጉሪቷ የዓለም ዓቀፍ ንግድ ድርሻ 6 በመቶ ነበር ብለዋል።

በቅርቡ በተደረገ ጥናት ግን ይህ አሃዝ ወደ 2 ነጥብ 8 በመቶ መውረዱንና ይህም አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን አመላካች ነው ይላሉ።

ችግሩን ለመቀልበስም በዋናነት የአፍሪካዊያን የእርስ በርስ ንግድና ቀጣናዊ ንግድ የበለጠ መጠናከር ይኖርበታል ነው ያሉት።

ይህ ብቻ ሳይሆን እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች ወደ ውጭ መላክና የሚላኩ ምርቶችን ማብዛትም አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

በአህጉሪቷ የሚገኙ ኩባንያዎችም ቢሆኑ የኢንዳስትሪ ግብዓቶችን ከውጭ አገራት የሚያስገቡ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአፍሪካ ቀጣናዊና አህጉራዊ የእርስ በርስ ንግድ ጠንካራ ቢሆን ኖሮ ይህ ጉዳይ ችግር ሊሆን አይችልም ነበር ብለዋል አምባሳደር አልበርት።

በቀጣይ የተሻለ አህጉራዊ የእርስ በርስ ንግድ ማጠናከር ችላ ሊባል የማይገባው አይነተኛ ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም