ቱኒዚያ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ሶስቱን አገራት ሊያቀራርብ በሚያስችል መልኩ እንደምትሰራ ገለጸች

147

ጥር 26/2014/ኢዜአ/ ቱኒዚያ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽን ሊያቀራርብ በሚያስችል መልኩ እንደምትሰራ መግለጿን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስታወቁ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤  ከቱኒዚያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  ኦትማን ጄናርዲ፣ ከሞሮኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናስር ቡሪታና ጋር ውይይት አድርገዋል።

አምባሳደር ዲና ዛሬ በሰጡት መግለጫ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከአገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል ብለዋል።

ከቱኒዚያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦትማን ጄናርዲ ጋር በነበራቸው ውይይት ቱኒዚያ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽን ሊያቀራርብ በሚያስችል መልኩ ለመሥራት ፍላጎት እንዳላት መግለጿን ተናግረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ ቱኒዚያ በአረብ ሊግ መድረክ ለሌላው ወገን የሚያዳላ አቋም ማሳየቷን አስታውሰው፤ ይህም የኢትዮጵያን ጥቅም የነካ እንደነበር ተናግረዋል ሲሉ ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።

የቱኒዚያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አገራቸው በቀጣይ ሶስቱን አገራት ሊያቀራርብ በሚያስችል መልኩ እንደምትሰራ መናገራቸውንም ነው የገለጹት፡፡

ከሞሮኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በነበራቸው ቆይታ ደግሞ ሁለቱ አገራት ይበልጥ ተቀራርበው መስራት በሚያስችላቸው ጉዳይ ላይ መክረዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያና ሞሮኮ በግብርና ቱሪዝምና በቴክኖሎጂ መስክ በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ መድረሳቸውን ጠቅሰው በአጭር ጊዜ ውስጥ የጋራ ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ትግበራ እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል።

ከሞሮኮ ጋር ያለውን ግንኙነትም ሁለቱ አገራት ተቀራርበው ለመስራት ፍላጎት ማሳየታቸውን አንስተዋል።

በሌላ በኩል የአፍሪካ የሰብዓዊና የሰዎች መብቶች ኪሚሽን ሊቀ-መንበር  ሬሚ ሉምቡ ጋር ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህም በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጋራ ጥናት አድርገው ሪፖርት መቅረቡን በመተለከተ መነሳቱን ተጠቁሟል።

በምርመራ ሂደቱ በጋምቢያ ዋና ከተማ ባንጁል የሚገኘው የአፍሪካ የሰብዓዊና  የሰዎች መብት ኮሚሽን እንዲሳተፍ ጥሪ ቢደረግለትም አለመሳተፉን ተናግረዋል።

በአማራና አፋር ክልሎች አሁንም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲመለከትና ውጤታማ እንዲሆንም ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር እንዲሰራ ተነግሮታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም