ባህሎችና ቋንቋዎች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ በምርምርና ጥናት ሊደገፉ ይገባል_የፌዴሬሽን ምክር ቤት

67

ዲላ፤ ጥር 26/2014 (ኢዜአ)...በሀገሪቱ የሚገኙ ባህሎችና ቋንቋዎች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ በምርምርና ጥናት ሊደገፉ እንደሚገባ የፌደሬሽን ምክር ቤት አስገነዘበ።

የጌዴኦ ብሔር ዘመን መለወጫ የዳራሮ በዓል አካል የሆነ የቋንቋና ባህል ሲምፖዚየም በተለያዩ ዝግጅቶች ዛሬ በዲላ ከተማ ተካሂዷል።

በሚኒስትር ማዕረግ የፌደሬሽን ምክር ቤት የህገ መንግስት ትርጉምና የውሳኔ አፈጻጸም ቋሚ ኮሚቴ ጸሃፊ ወይዘሮፀሃይ ወራሳ በወቅቱ እንደገለጹት ባህሉና ቋንቋው የተከበረለት ህዝብ በሀገራዊ ልማት ላይ የላቀ ተሳትፎ ለማበርከት ይበልጥ እንዲነሳሳ ያደርጋል።

ብሔር ብሔረሰቦች በህገ መንግስቱ የተሰጣቸውን ባህልና ቋንቋቸውን የማልማት መብት እንዲጠቀሙ ምክር ቤቱ በቅርበት እገዛ እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል። 

የህዝቦች ባህልና ቋንቋ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ በምርምርና ጥናት ሊደገፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በዚህ ረገድ የጌዴኦ ብሔር የቋንቋና ባህል ሲምፖዝየም የብሔሩን ባህል በተለይም የዳራሮ የዘመን መለወጫ በዓል በማጥናት ከሀገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ አስተዋጾ እንደሚኖረው አመልክተዋል።

ጌዴኦ ከ500 ዓመታት በላይ እራሱን በባህላዊ ስርዓት በማስተዳደር ለዘመናዊ የመንግስት ስርዓት አቅም መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ ዶክተር ዝናቡ ወልዴ ናቸው።

በራሱ ዘመን አቆጣጠር አዲስ ዓመት የሚቀበልበት የዳራሮ በዓል የባህላዊ ስርዓቱ መገለጫ መሆኑን አስረድተዋል።

የብሔሩ መገለጫ የሆኑ ባህሎች በተለይ የአካባቢ ጥበቃ የባቦ ሥርዓቱና ቋንቋው ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ የዞኑ መንግስት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

"ቋንቋው የሳይንስ ቋንቋ እንዲሆን ምርምርና ጥናቶች እየተሰሩ ነው" ያሉት ምክትል አስተዳዳሪው በዞኑ የሚገኙ ከ500 በላይ ባህላዊ ሥርዓቶች የሚካሄዱባቸው ስፍራዎች እንዲጠበቁ መደረጉን አመልክተዋል።

የጌዴኦ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ ዮሴፍ ማሩ በበኩላቸው ጌዴኦ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ፋይዳ ያላቸው ሀገር በቀል እውቀቶች ባለቤት መሆኑን ገልጸዋል።

 የአካባቢ ጥበቃ ባህሉን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት በ(ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ  እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ባህላዊ እሴቶችን በማስጠናትና መሰል ሲምፖዚየሞችን በማዘጋጀት የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በዛሬው መድረክ ስድስት የጥናት ውጤቶች ቀርበውውይይት እንደተደረገባቸውና ለቀጣይ ስራ ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦች መወሰዳቸውን ጠቁመዋል።

ጌዴኦ በምትኩ ችግኝ ሳይተከል ዛፍ ያለመቁረጥ ባህላዊ የባቦ ስርዓቱ አካባቢው ተጠብቆ እንዲቆይ ምክንያት መሆኑን ያነሱት ደግሞ በሲምፖዚየሙ "የአረንጓዴው መልካ ምድር ተስፋና ፈተናዎች" በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት ዶክተር ታደሰ ኪጴ ናቸው።

የብሄሩየባህላዊ ትሩፋት የሆነው የጥምር ግብርና ሥርዓቱ ከህዝብ ቁጥር መብዛትና መሰረታዊ ፍላጎቶች መጨመር ጋር ተያይዞ ችግር ውስጥ መግባቱን ጠቅሰዋል።

ባህላዊ ሥርዓቱ ትውልድ እንዲጠብቀው ግንዛቤ የማስጨበጫ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው አመልክተው፤ የጥምር ግብርና ቱሪዝምና የካርበን ተጠቃሚነት ላይ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል።

በመድረኩ ላይ የፌዴራልናበየደረጃውየሚገኙየስራሃላፊዎች፣ አባገዳዎች፣ የባህላዊ የባሌ ስርዓት መሪዎች፣የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሁራንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም