በአፋር በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች ከ22 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ ተደረገ

59

ሰመራ ጥር 25/2014 (ኢዜአ ) በአፋር ክልል አሸባሪው ህወሃት በፈጸመው ወረራ ለተጎዱ ወገኖች ከ22 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ ተደረገ።

በአዲስ አበባ የሚገኙ የክልሉ ተወላጆች ከተለያዩ ወገኖች በማሰባሰብ ድጋፉን ማድረጋቸው ተመላክቷል።

በአዲስ አበባ የተቋቋመው ሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ወይዘሮ ዘሀራ ሁመድ ድጋፉን አስረክበዋል ።

ምክትል አፈ ጉባኤዋ በወቅቱ እንደገለጹት የአፋር ህዝብ ለሀገሩ የከፈለው ውድ የህይወት ዋጋ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያኮራና ለደረሱ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመቶች ወገናዊ አጋርነቱን እንዲያሳይ ያደረገ ነው።


በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና የግል ድርጅቶች እንዲሁም ግለሰቦች ለአፋር ወንድም ህዝብ ድጋፍ ማድረጋቸውን አመልክተዋል ።

ከድጋፉ  ውስጥ 10 ሚሊየኑ በጥሬ ገንዘብና ቀሪው በአይነት የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።



በአይነት የተደረገው ድጋፍ የዳቦ ዱቄት፣ የምግብ ዘይት፣ ማካሮኒና ፓስታ ጨምሮ  ፍራሽ፣ አልባሳትና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

 ከተለያዩ አጋር አካላት ድጋፍ በማሰባሰብ ለተጎጂዎች የማድረስ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል አፈ ጉባኤዋ አመላክተዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የክልሉ ርእሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ ሁሉም ኢትዮጵያዊ   በክልሉ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ እያደረገ ያለው ርብርብ  የሚያኮራ ነው።

በአዲስ አበባ የሚገኙ የክልሉ ተወላጆች የወገናቸው ጉዳት እረፍት ነስቷቸው ከተለያዩ አጋር አካላት በማሰባሰብ ለተጎጂ ወገኖች ያደረጉት ድጋፍ ችግሮችን የሚያቃልል መሆኑን አመልክተዋል።

ስለ ተደረገው ድጋፍ በክልሉ መንግስትና በተጎጂ ወገኖች ስም አመስግነው " መተባበር፣ መረዳዳቱና አንድነቱ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል" ብለዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም