የፈጠራና ቴክኖሎጂ መነሻ ሃሳቦችን ለማልማትና የኢኖቬሽን ምህዳሩን ለማስፋፋት የፖሊሲ ማሻሻያ እየተሰራ ነው

126

ጥር 26/2014/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ የፈጠራና ቴክኖሎጂ መነሻ ሃሳቦችን ለማልማትና የኢኖቬሽን ምህዳሩን ለማስፋፋት የፖሊሲ ክለሳና የማሻሻያ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ ከፈጠራ ባለሙያዎች እና ስራ ፈጣሪዎች ጋር አገር አቀፍ የምክክር እና የልምድ ልውውጥ መድረክ በዛሬው እለት አካሂዷል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ፤ የፈጠራ ሃሳብን እና ኢኖቬሽንን በማበረታታት፣ በመደገፍ እና ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የፈጠራ ሃሳብ ወደ እሴት እንዲለወጥ ለማድረግ ሚኒስቴሩ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ የስራ ፈጠራ መነሻ ሃሳቦች (ስታርታፖች)፣ የፈጠራ ባለሙያዎች እና ስራ ፈጣሪዎች ዋነኛ ተዋናዮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የፈጠራ ስራዎች እና የቴክኖሎጂ ማበልጸጊያ ማዕከላት፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፉ የመንግስት ተቋማት እንዲሁም አጠቃላይ የኢኖቬሽን ሥርዓተ ምህዳር ገንቢዎች ሚናም ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።

ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ዕውቅት እና ሃብት ያመነጩ ትላልቅ ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶችና ተቋማት ለዕድገታቸው መሰረት ትልቁን ድርሻ ከሚይዙ ዘርፎች መካከል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ አንዱ እና ዋነኛው ሆኖ ይጠቀሳል።

ኢኖቬሽንን የሚያለሙ የቴክኖሎጂ መነሻ ሃሳቦች ሰፊ የስራ ዕድልን፣ የዘመነ ምርትንና አገልግሎትን የሚፈጥሩ፤ ከፍተኛ ሀብት ፈጣሪዎች እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያሳድጉ ናቸው ብለዋል።

በመሆኑም በኢኖቬሽን ልማት ምህዳር ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

በዚህም የፈጣና የቴክኖሎጂ መነሻ ሃሳቦችን (ስታርታፖችን) መደገፍ የወደፊቱን ትላላቅ ኢንዱስትሪዎችን መፍጠር እንደሆነ የሚታመን በመሆኑ፤ ዘርፉ ከአገር የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

መንግስት የፈጠራ እና የቴክኖሎጂ መነሻ ሃሳቦችን እና የኢኖቬሽን ምህዳር ገንቢዎችን በቅርበት ለመከታተል እና ለመደገፍ ያሉ ችግሮችን በመለየት እና በመፍታት ጠንካራ አቋም ይዞ የትግበራ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

በዚህም የፈጠራ እና ቴክኖሎጂ መነሻ ሃሳቦች ልማት እና የኢኖቬሽን ምህዳር ገንቢዎችን መስፋፋት ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲን የመከለስና የማሻሻል ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።

የፈጠራ እና ቴክኖሎጂ መነሻ ሃሳብ አመንጪዎችን ዕውቅና ከመስጠት ጀምሮ ለፈጠራ ስራ የሚያግዝ አዋጅና የኢኖቪሽን ፈንድ ሥርዓት እየተበጀ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በቅርቡ የ2021 ዓለም ዓቀፍ የፈጠራ ምጣኔ (Global Startup index 2021) ከፍተኛ ደረጃ ካላቸው 100 አገራት ዝርዝር ውስጥ መካተቷንም አስታውሰዋል።

በመሆኑም አገሪቷ የሰው ኃይል እና የተፈጥሮ ሃብቷን በአግባቡ በመጠቀም ዘርፉ ለአገራዊ ዕድገት የሚጫወተውን ሚና ለማጎልበት ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

በዚህ ረገድ የግሉ ዘርፍ በምርምር፣ በቴክኖሎጂ እና በኢኖቬሽን ልማት መሪነቱን እንዲይዝ የሚችልበት አቅም ላይ ለማድረስ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊስ እና የብሔራዊ የሳይንስና ቴክኖሎጂ አዋጅ በቅርቡ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም፤ የፈጠራ እና ቴክኖሎጂ መነሻ ሃሳቦችን ከማልማት አንፃር በኢኖቬሽን ሥነ-ምህዳር ውስጥ ስላለው ኃላፊነትና ሚና እንዲሁም ስኬት እና ተግዳሮቶች ዙሪያ የልምድ ልውውጥ አድርገዋል።

በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ያሉ የፈጠራ እና ቴክኖሎጂ መነሻ ሃሳብ አመንጪዎች ባሉበት ቦታ ሆነው የውድድር ማመልከቻ የሚሞሉበት፣ የሚወዳደሩበት፣ ውጤታቸውን የሚከታተሉበት እንዲሁም መረጃ የሚያገኙበት ፖርታል በይፋ ተመርቋል።

የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፍ በዘላቂ የልማት ግቦች፣ የአፍሪካ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ስትራቴጂ 2024 እና በአፍሪካ አጀንዳ 2063 እንዲሁም በኢትዮጵያ “የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ስትራቴጂ መተግበር እና ስኬታማ ማድረጊያ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም