በአዳሚ ቱሉ 14 የአሸባሪው ሸኔ አባላት በሰላም እጃቸውን ሰጡ

381

አዳማ፣  ጥር 26/2014/ኢዜአ/— በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳ በሰላም እጃቸውን የሰጡ 14 የአሸባሪው ሸኔ አባላት ትናንት በምህረት ከማህበረሰባቸው ጋር ተቀላቀሉ።

የአሸባሪው ሸኔ አባላት በሰላም እጃቸውን ሰጥተው በምህረት ማህበረሰባቸው የተቀላቀሉት በመንግሥት፣ አባ ገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች የተደረገላቸውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ነው።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ እንደገለጹት እጃቸውን የሰጡ ወጣቶች ከሽብር ቡድኑ ጋር ተሰልፈው ለፈፀሙት የጥፋት ተግባር ተፀፅተው ማህበረሰባቸውን ይቅርታ ጠይቀዋል።

የመንግሥትና የአባ ገዳዎችን ጥሪ ተቀብሎ ከአሸባሪው የሸኔ የጥፋት መንገድ የሚመለስ ማንኛውንም የተደራጀ ቡድንም ሆነ አካላት ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

የአሸባሪው ሸኔ አጀንዳ ለኦሮሞ ህዝብና ለሀገር የማይጠቅም መሆኑን ተገንዝበው የሽብር ቡድኑ የጥፋት ማስፈፀሚያ መሳሪያ ላለመሆን ወስነው ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለሳቸውን አመልክተዋል።

መንግሥት በሰላማዊ መንገድ ወደ ህብረተሰቡ የተቀላቀሉ ወጣቶች በልማት፣ በአካባቢ ሰላምና ፀጥታ ማስከበር ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን እንደሚያመቻችም አረጋግጠዋል።

የአዳሚ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሙሐመድ በሪሳ በበኩላቸው አሸባሪው ሸኔ ሰላማዊ ዜጎችን በመግደልና ሀብት በማውደም ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን እየፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህን እኩይ ድርጊቱን በተግባር ያረጋገጡት ወጣቶች ሸኔ የኦሮሞን ህዝብ የማይወክል የጥፋት ቡድን ስብስብ መሆኑን ተገንዝበው የሰላም ጥሪውን ተቀብለው  ማህበረሰቡን በምህረት ተቀላቅለዋል ብለዋል።

አብዱልቃድር ገና እንዳለው የኦሮሞ ህዝብ በራሱና ልጆቹ በከፈሉት መሰዕዋትነት ነፃነት አግኝቷል።

አሸባሪው ሸኔ ከወያኔ ጋር ግንባር ፈጥሮ ሀገር ለማፍረስ መነሳቱ ኦሮሞን እንደማይወክል ተገንዝበው የመንግሥትና አባገዳዎችን ጥሪ ተቀብለው ወደ ህዝቡ መመለሳቸውን ተናግሯል።

የሸኔ ዓላማ የኦሮሞ ህዝብ ከሚፈልገው ሰላምና ልማት በተቃራኒ በመሆኑ በድርጊታቸው ተፀፅተው መመለሳቸውን ሌንጮ ሮባ  ገልጿል።