መስህቦችን የቱሪስት መዳረሻዎች ለማድረግ እየተሰራ ነው -የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ

264

ደብረ ታቦር ፣ ጥር 26/2014(ኢዜአ) በደቡብ ጎንደር ዞን መስህቦችን በመጠበቅና በማልማት አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በትብብር እየተሰራ መሆኑን የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

የዩኒቨርሲቲው የውጭ ግንኙነትና ስትራቴጂክ አጋርነት ዳይሬክተር ዶክተር አብርሃም መልኬ ለኢዜአ እንደገለጹት ዞኑ በርካታ የቱሪስት መስህቦች ቢኖሩትም በአግባቡ ለምተው ጥቅም እያስገኙ አይደለም።

“በዞኑ የአፄ ቴዎድሮስ ሴባስቶፖል መድፍ የተሰራበት ሥፍራ፣ የጉና ተራራ ጥብቅ ደንና ሌሎች መስህቦች ቢኖሩም በሚገባው ልክ ለምተው፣ ተጠብቀው ተዋውቀው ቱሪስቶች እንዲጎበኟቸው አልተደረገም “ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ጥናትና ምርምር በማድረግና መስህቦቹን የቱሪስት መዳረሻዎች ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በየዓመቱ የሚካሂደውን የበጌምድር ፈረሰኞች ማህበር የፈረስ ጉግስ ውድድር የቱሪስት መስህብ  እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

“በየዓመቱ የሚካሄደው ውድድር የውጭና የአገር ውስጥ ቱሪስቶችን እንዲስብ በቀጣይ የውድድር ፈረሶችን በማዘጋጀትና የጋላቢዎችን አቅም ለማጎልበት ትኩረት ይሰጣል” ብለዋል።

የደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዳነ ደምሴ በበኩላቸው የአካባቢውን ቱሪዝም ለማነቃቃትና ለማስተዋወቅ ከደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲና ከሌሎች አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የጉና በጌምድር ፈረሰኞች ማህበር የሚያካሂደው የጉግስ ውድድር አንዱ ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል።

ውድድሩ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በድምቀት እየተከበረ መሆኑን አስታውቀዋል።

“ጽህፈት ቤቱ የጉና በጌምድር የፈረሰኞች ማህበር የፈረስ ጉግስ ውድድርን የቱሪስት መስህብ በማድረግ ገቢውን እንዲያሳድግና የራሱ የመወዳደሪያ ሜዳ እንዲኖረው ከፋርጣ ወረዳና ከደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ጋር እየሰራ ይገኛል” ብለዋል።

የጉና በጌ ምድር የፈረሰኞች ማህበር ከተመሰረተ 74ኛ ዓመቱን እንዳስቆጠረ የገለጹት ደግሞ የማህበሩ አስተባባሪ አቶ ሙሉጌታ መንበር ናቸው።

ማህበሩ እንደ አገው የፈረሰኞች ማህበር በኢኮኖሚ ጠንክሮ እንዲወጣና በቅርስነት እንዲመዘገብ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጥያቄ መቅረቡን ተናግረዋል።

ማህበሩ በአሁኑ ወቅት አንድ ሺህ የሚጠጉ አባላት እንዳሉትና የአባላቱን ቁጥር በእጥፍ ለማሳደግ እንደሚሰራ አስረድተዋል።

ማህበሩ በገቢ ራሱን እንዲችል በአዲስ መልክ እየተደራጀ እንደሆነም አስታውቀዋል።