የኦሮሚያ የወጣቶች አደረጃጀት በክልሉ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለተጎዱ ወገኖች የገቢ ማሰባሰቢያ አካውንት ይፋ አደረገ

151

አዲስ አበባ፣  ጥር 26/2014(ኢዜአ) የኦሮሚያ የወጣቶች አደረጃጀት በክልሉ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ የሚሆን የገቢ ማሰባሰቢያ አካውንት ይፋ አደረገ።

የኦሮሚያ የወጣት አደረጃጀት በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ የተዘጋጀውን እንቅስቃሴ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የኦሮሚያ ወጣቶች ሊግ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ሮዛ ቢያ፤ በመግለጫው ላይ እንዳለችው በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች የተከሰተው የድርቅ አደጋ  ዜጎችን ለከፍተኛ ችግር ዳርጓል።

በድርቁ ለተጎዱ ወገኖች ለመድረስ በመንግስትና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም ግለሰቦች በጥረት ላይ መሆናቸውን ጠቅሳለች።

የኦሮሚያ ወጣቶች ሊግ፣ ማህበርና ፌዴሬሽንም በጋራ በመሆን ወጣቱን የሚያንቀሳቅስ የገቢ ማሰባሰቢያ እቅድ አዘጋጅተው ወደ ስራ መግባታቸውን ገልፃለች።

“200 ብር በድርቅ ለተጎዱ ወገኖቻችን” በሚል መሪ ሃሳብ  በተለያዩ የስራ ዘርፎች የተሰማሩና በትምህርት ተቋማት ላይ ያሉ ወጣቶችን በማሳተፍ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ ታቅዷል ብላለች።

ይህንን ለማስተባበር የተቋቋመው ኮሚቴ የሚያንቀሳቅሰው አካውንት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሂሳብ ቁጥር 1000454103417 መከፈቱን ጠቅሳ የቻሉ ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቃለች።

በሳምንት ጊዜ ውስጥ የታሰበውን ገንዘብ ለማሰባሰብ መታቀዱን ገልፀው ገንዘቡ ለታለመበት ዓላማ እንዲውል ወጣቶች የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

በመላ ኢትዮጵያ ያሉና በውጭ አገራት የሚኖሩ ወገኖች ሁሉ ይህንኑ መልካም ተግባር በመቀበል የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።

ወጣቶች በአገር ደረጃ ስጋት ደቅኖ የነበረውን የህልውና ዘመቻ በድል በመወጣት ያሳዩትን ቁርጠኝነት የማህበረሰብ ችግሮችንም በመፍታት አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ኃላፊዋ ጠይቃለች።

በዝናብ እጥረት ሳቢያ የተከሰተው ድርቅ ያስከተለውን ጉዳት ለመመልከት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን እና በሶማሌ ክልል ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወቃል።