ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በአፍሪካ ዋንጫ ባሳየው የዳኝነት ብቃት አድናቆት እየተቸረው ነው

286

ጥር 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በአፍሪካ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ባሳየው የዳኝነት ብቃት በርካታ ተከታዮች ባሏቸው የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች ጭምር አድናቆት እየተቸረው ነው፡፡

ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ በቡርኪናፋሶና ሴኔጋል መካከል የተደረገውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት በብቃት መርቷል።

በጨዋታው ሴኔጋል ቡርኪናፋሶን 3 ለ 1 በሆነ ውጤት በመርታት ለፍጻሜ ማለፍ ችላለች።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ውጥረት የበዛበትና በብዙ ንክኪ የታጀበውን ጨዋታ በተረጋጋ መንፈስና በብልጠት የመራ ሲሆን፤ በዚህም ከፍተኛ አድናቆት እየተቸረው ይገኛል፡፡

በርካታ ተከታዮች ያሉት “ዴይሊ ሜል” የተሰኘው የመገናኛ ብዙኃን አውታርን ጨምሮ “ጎል አፍሪካ” ፣”ኤኤፍጂ”፣ “አፍሪካን ሶከር ዞን” እና ሌሎች መገናኛ ብዙሃን ኢንተርናሽናል ዳኛ በግማሽ ፍጻሜው ያሳየውን ብቃት እያወደሱት ይገኛሉ፡፡

ዴይሊ ሜል በዘገባው የአፍሪካ ምርጡ ዳኛ ሲል ያሞካሸው ሲሆን፤ ዳኞች ከእርሱ ልምድ መቅሰም እንዳለባቸው አትቷል፡፡

ኤኤፍጂ የተባለው የእግር ኳስ ድረ-ገጽ በበኩሉ “አስደናቂ ብቃት” ሲል ሙገሳ ችሮታል።

በተመሳሳይ ሌሎች የእግር ኳስ ቤተሰቦችም ኢንተርናሽናል ዳኛ በጨዋታው ላሳየው የራስ መተማመንና ሚዛናዊ ዳኝነት አድናቆትና ሙገሳን እየቸሩት ነው።

የአፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜን ጨዋታን ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ መምራት አለበት የሚሉ ሃሳቦችም በስፋት እየተሰራጩ ነው፡፡

በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያዊው ዳኛ ባምላክ ተሰማ ሴኔጋል ከጊኒ እንዲሁም ካሜሩን ከኮሞሮስ ያደረጉትን ጨዋታ በዋና ዳኝነት መምራቱ ይታወቃል፡፡፡

በተጨማሪ በውድድሩ የ”ቫር” ወይም በምስል ምልከታ ዳኝነት ላይ ተሳትፎ አድርጓል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼