በቦረና ዞን የተከሰተውን የድርቅ አደጋ ለመቋቋም የመላ ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ ያስፈልጋል

67

ጥር 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) በቦረና ዞን የተከሰተው የድርቅ አደጋ በነዋሪዎች ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት በመቀነስ ችግሩን ተቋቁሞ ለማለፍ የመላ ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የቦረና አባ ገዳ ጥሪ አቀረቡ። 

የቦረና አባ ገዳ ኩራ ጃርሶ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በአካባቢው ዝናብ ለረጅም ወራት ባለመዝነቡ የከፋ የድርቅ አደጋ በመከሰቱ ሰዎችና እንስሳት ለችግር ተዳርገዋል።

እስካሁንም የድርቁ ሁኔታ እየተባባሰ በመምጣቱ በተለይም በእንስሳት ላይ ከፍተኛ አደጋ መደቀኑን ተናግረዋል።

የቦረና ህዝብ በድርቁ ምክንያት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል ያሉት አባ ገዳ ኩራ ጃርሶ፤ ይህን አስቸጋሪ ጊዜ ለማለፍ የመላ ኢትዮጵያዊያን የተጠናከረ ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

የአካባቢው ህዝብ አኗኗር ከእንስሳት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑን ገልጸው ድርቁ ከአሁኑም የከፋ ጉዳት ሳያስከትል እንደጋገፍ፣ እንተጋገዝ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

መንግስት የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ መሆኑን ጠቅሰው የሌሎችም አካላት ድጋፍ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የድርቁን አደጋ ለመከላከል መንግስትና ህዝቡ እንዲሁም ግለሰቦች እስካሁን ላደረጉት ድጋፍ አባ ገዳ ኩራ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም በመንግስት በኩል የተለያዩ ጥረቶች በመደረግ ላይ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፤ በዛሬው እለት በአካባቢው ተገኝተው ድርቁ ያስከተለውን ጉዳት ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም