ወጣቶች የአገራቸውን ህልውና ለማስጠበቅ መከላከያ ሠራዊትን መቀላቀል አለባቸው

69

ሆሳዕና፣ ጥር 25/2014 (ኢዜአ) ወጣቶች የአገራቸውን ህልውና ለማስጠበቅ መከላከያ ሠራዊትን እንዲቀላቀሉ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የአሁንና የቀድሞ አባላት አስገነዘቡ ።

የአየር ኃይሉ አባላት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት አስተያየት እንዳመለከቱት ወጣቶች ሠራዊቱን በመቀላቀል ነጻነቷንና አንድነቷን ጠብቃ የኖረች ኢትዮጵያን  ህልውና ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል።

ከአባላቱ መካከል ሻለቃ ሺፈራው ሳዊቾ ኢትዮጵያ ነጻነቷን አስጠብቃና ተከብራ የኖረችው ዜጎች ለዘመናት ባደረጉት ተጋድሎ መሆኑን አውስተዋል።

ወጣቶች  መንግሥት መከላከያ ሠራዊትን እንዲቀላቀሉ ያቀረበውን ጥሪ በመቀበል ለአገራቸው ህልውና መረጋገጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል ።

"በተለያዩ ጊዜያት አገሪቱ የገጠሟትን የህልውና አደጋዎችና የተቃጡብን ጫናዎች በሉዓላዊነትና በአገር ጉዳይ የማንደራደር መሆናችንን አሳይተናል "ያሉት ደግሞ ሌላው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባል ሻለቃ ከበደ አቦ ናቸው ።

"ወጣቱ ትውልድ አገሩ በአፍሪካ ቀንድ ያላት አቀማመጥ፣በቅኝ ገዢዎች ያለመገዛቷንና የአካባቢውን መልካ ምድራዊ  ፖለቲካን  በመረዳት ህልውናዋን ለማስከበር ዝግጁ መሆን አለበት" ብለዋል።

ትውልዱ በውትድርና ዘርፍ በመቀላቀል ነፃነቷ የተጠበቀ አገር ለተተኪው ትውልድ በማስተላለፍ የራሱን ታሪክ እንዲያስመዝግብ አሳስበዋል።

''የእናት አገራችንን ህልውና አስጠብቆ ለማስቀጠል ከእኛው ውጭ የሚመጣ አካል የለም'' ያሉት ደግሞ የቀድሞ የአየር ኃይል አባል ገብረ ማርያም ጫሚሶ ናቸው።

በውትድርና ሀገርን ማገልገል  ክብር መሆኑን የተናገሩት አስተያየት ሰጪው ወታደርነት የዳበረ ስብዕናና የአዕምሮ ብስለት ያለው ዜጋ ለመሆን እንደሚያስችል አመልክተዋል።

ወጣቶች የኢትዮጵያ ህልውናን ለማስጠበቅ ሠራዊቱን በመቀላቀል የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም