ከፍተኛ የቧንቧ መስመር ቆርጠው ስርቆት የፈጸሙ በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ

68

ነገሌ፣ ጥር 25/2014- (ኢዜአ ) ከፍተኛ የቧንቧ ውሀ መስመር በመቁረጥ ስርቆት የፈጸሙ ሁለት ግለሰቦችን እስከ አራት አመት በሚደርስ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ።

የምእራብ ጉጂ ዞን የገላና ወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሁሴን ገጃ  ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቦቹ የቆረጡትን የቧንቧ መስመር ለመሸጥ ሲያጓጉዙ እጅ ከፍንጅ መያዛቸው  በአቃቢ ህግ ማስረጃ በመረጋገጡ ቅጣቱ ተወስኖባቸዋል ።

በወረዳው ቀርሳና ምርጋኖ ቀበሌዎች በግለሰቦቹ የተቆረጠው ከፍተኛ መስመር ለበርካታ የገጠር ከተሞች ውሀ የሚከፋፈልበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የቧንቧ መስመሩ 10 ሺህ 788 ብር የሚገመት እንደሆነ ከወረዳው ውሀ ቢሮ የተገኘ ማስረጃ በክስ መዝገቡ መካተቱን ጠቅሰዋል፡፡

ግለሰቦቹ ለተከሰሱበት የከባድ ስርቆት ወንጀል  የመከላከያ ምስክር ማቅረብ ባለመቻላቸው የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቱ ጥር  25 ቀን 2014 ዓም ባዋለው ችሎት አንደኛ ተከሳሽ ባቲ አራርሶ በ4 አመት ጽኑ እስራት እንዲሁም ሁለተኛ ተከሳሽ መኙርቲ ጀልዶ  በ3 አመት ጽኑ እስራትና በ3 ሺህ ብር እንዲቀጡ መወሰኑን  ፕሬዝዳንቱ  አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም