ኢትዮጵያ ተጋርጦባት የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ጫና ማለፍ የቻለችው በአፍሪካውያን እገዛ ነው

94

ጥር 26፣ 2014 (ኢዜአ) “ኢትዮጵያ ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ እና አንዳንድ ሀገራት ተጋርጦባት የነበረውን ከፍተኛ ጫና ማለፍ የቻለችው በአፍሪካውያን እገዛ ነው” ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

አቶ ደመቀ ይህን ያሉት ትናንት ምሽት 40ኛው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባኤን ለመታደም ለተገኙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና የዲኘሎማቲክ ማህበረብ አባላት የእራት ግብዣ ባደረጉበት ወቅት ነው።

በአዲስ አበባ ከሚካሄደው የአፍራካ ህብረት የመሪዎች የአካል ስብሰባ ቀደም ብሎ የሚካሄደው የአባል ሃገራቱ 40ኛው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በትናንትናው እለት መጀመሩ ይታወሳል።

በስነ-ስርአቱ ላይ አቶ ደመቀ መኮንን ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ እና አንዳንድ ሀገራት ተጋርጦባት የነበረውን ከፍተኛ ጫና ማለፍ የቻለችው በአፍሪካውያን እገዛ ነው ብለዋል።

የተቀናጀውን የአንዳንድ አለምአቀፍ ተቋማት እና ሀገራት ፀረ ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ በአፍሪካውያን ወንድማዊ ድጋፍ ማሸነፍ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተጠርቶ የነበረው የጄኔቫው ጉባኤ የዚህ ማሳያ መሆኑን አንስተው፤ “ልዩ ጉባኤው የአንድም አፍሪካ ሀገርን ድጋፍ እንዳላገኘ ገልጸው፤ ይህም የአፍሪካውያን ምን ያህል ከኢትዮጵያ ጎን እንደቆሙ አሳይተዋል” ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ ኢትዮጵያዊያን በድምፃቸው መንግስታቸውን መምረጣቸውን አስታውሰው፣ ተመራጩ መንግስት ከቀደሙት በተለየ በካቢኔው ውስጥ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማቀፉን በንግግራቸው ጠቅሰዋል።

ሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርአትን ለማስፈን ተከታታይ እርምጃዎችን እየወሰደች ሲሆን በቅርቡ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን መፍታቷን አንስተዋል።በተግዳሮቶችም ውስጥ ሆና ኢትዮጵያ የህዝቦቿን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማረጋገጥ እየጣረች እንደምትገኝ ያመለከቱ ሲሆን ለዚህም የታላቁ የኢትዮጵያ ህደሴ ግድብን እንደ ማሳያ ጠቅሰዋል።ተለዋዋጭ በሆነው አለምአቀፍ ጉዳዮች አፍሪካ ተገቢ ስፍራ እንዲኖራት ብዙ መሰራት እንዳለባት የጠቀሱት አቶ ደመቀ፤ ለዚህም ስኬት ኢትዮጵያ አብዝታ እንደምትሰራ ማስገንዘባቸውን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።አቶ ደመቀ የተባበረች እና የበለፀገች አፍሪካ እውን እንድትሆን ሁሉም የህብረቱ አባል ሀገር እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም