በፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ችግር ፈቺ የሆኑ ቴክኖሎጂያዊ ፈጠራዎችና ምርምሮች ተገኝተዋል

553

ጥር 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) በፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ በውሃ፣ በምግብ ኢነርጂ፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በመልካም አስተዳደርና በሰው ሃብት ልማት እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች አፍሪካዊ የሆኑ ችግር ፈቺ ውጤቶች መገኘታቸው ተገለጸ።

የአፍሪካ ሕብረት 40ኛዉ የስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ጉባኤ የሕብረቱ አባል ሀገራት ሚኒስትሮችና የአህጉሩ ልዩ ልዩ ተቋማት ሀላፊዎች በተገኙበት በአፍሪካ ሕብረት በመካሄድ ላይ ነው።

በአፍሪካ ሕብረት የትምህርት፣ ሳይንስና፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ሞሐመድ ቤልሆሲን በዚህ ወቅት በሰጡት መግለጫ ኮሚሽኑ የትምህርት ጥራትን፣ ተደራሽነትንና ቴክኖሎጂያዊ ስኬቶችን ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተለይም የፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ጽንሰ ሃሳብ ከተጠነሰሰበት እ.አ.አ ከ2008 ጀምሮ ትምህርትን በከፍተኛ ጥራት የሚሰጡ፣ በቴክኖሎጂ የታገዙ እና ስራ እድል ፈጠራን የሚያግዙ ተቋማትን ለማቋቋም እየሰራ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በፓን አፍሪካ  ዩኒቨርሲቲ ስር ባሉ ተቋማት በኩል በአምስት የተለያዩ የአፍሪካ ክፍሎች ማለትም በአልጄሪያ፣ ኬኒያ፣ ናይጄሪያ፣ ካሜሮን እና ደቡብ አፍሪካ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች ትምህርት  እየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

“በእነዚህ ተቋማት የውሃ፣ ኢነርጂ፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በመልካም አስተዳደርና በሰው ሃብት ልማት፤ ለግብርና ስራ የሚሆን መሬት ጥናት ጉዳዮች ላይ ምርምሮችን ጨምሮ አፍሪካዊ የሆኑ የስራ ፈጠራዎች፣ አዳዲስ ግኝቶችና የስነ ምግብ ውጤቶች ተገኝተዋል ብለዋል።

በሌላ በኩል በአፍሪካ ሕብረት 2063 አጀንዳ መነሻነት የኤሌክትሮኒክስ ትምህርት በርቀት የሚሰጥብት የፓን አፍሪካን ኤሌክትሪካል እና ቨርቹዋል ዩኒቨርሲቲ መመስረቱን ተናግረው፤ በየትኛውም ክፍል የሚገኙ አፍሪካውያን ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼