በክልሉ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ የሚውል ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር ተጀመረ

205

አሶሳ፣ ጥር 25 / 2014 ( ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ የሚውል ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር መጀመሩን በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ የሴቶች ሊግ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ ወይዘሮ ከልቱም አሸናፊ ለኢዜአ እንዳሉት በሊጉ አስተባባሪነት እስከ የካቲት 2014 ዓ.ም መጨረሻ የሚቆይ  “200 ለእናቴ” እና “አንድ ዕቃ ለአንድ ተፈናቃይ” በሚል መሪ ሀሳብ ገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር ተጀምሯል፡፡

ዓላማው በጦርነት የተጎዱን በተለይም ሴቶች፣ ህጻናትና አካል ጎዳተኞችን መልሶ ለማቋቋም እንደሆነ ገልጸው በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው መርሀ ግብር አካል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ 2 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ እንዲሁም 2 ሚሊዮን ብር ደግሞ በቁሳቁስ መልክ ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

መርሀ ግብሩ በተጀመረበት ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ከ120 ሺህ ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ሃላፊዋ ጠቁመዋል፡፡

ለእቅዱ ስኬት የክልሉ ህብረተሰብ የተለመደ ተሳትፎውን እንዲያደርግ የጠየቁት ወይዘሮ ከልቱም በተለይ የሊጉ አባላት በግንባር ቀደምትነት በማስተባበር የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

ወይዘሮ ነፊሳ ሙሳ የተባሉ የአሶሳ ነዋሪ የገቢ ማሰባሰብ መርሃ ግብሩ በተለይም ሴቶች እና ህጻናትን የሚደግፍ በመሆኑ ለስኬታማነቱ የድርሻቸውን ለማበርከት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

የግጭት ተጎጂዎችን መደገፍ በመንግስት ብቻ ሳይሆን በእኛም ጭምር ነው” ያሉት አስተያየት ሰጪዋ ቤኒሻንጉል ጉሙዝም የችግሩ ዋነኛ ተጎጂዎች ከሆኑ ክልሎች መካከል አንዱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እኛ በልተን እያደርን የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ሲራቡ በዝምታ የምንመለከትበት ጉዳይ አይኖርም የሚሉት ነዋሪዋ ” ህብረተሰቡ በድጋፍ ማሰባሰቡ ትብብሩን በማጠናከር ለወገን ደራሽ ወገን መሆኑን ማሳየት አለበት” ብለዋል፡፡