ሕዝቡ አሸባሪው ህወሓትን ያሸነፈበትን ወኔና ቁርጠኝነት በልማት መድገም አለበት

72

ደብረ ታቦር፣ ጥር 25/2014(ኢዜአ) የደብረ ታቦርና አካባቢው ሕዝብ አሸባሪው ህወሓትን ያሸነፈበትን ወኔና ቁርጠኝነት በልማቱም እንዲደግመው የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ጌታቸው ጀምበር አሳሰቡ።

የቅዱስ መርቆርዮስ ዓመታዊ  በዓልና የፈረስ ጉግስ ውድድር በደብረ ታቦር ከተማ በድምቀት ተከብሯል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት  አሸባሪው ቡድን በክልሉ ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት አድርሷል።

ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማፍረስ አስቦ ወደ ደብረ ታቦር ሲገሰግስ የአካባቢው ሕዝብ ከፀጥታ ሃይሎች ጎን በመቆም የጠላትን አከርካሪ በመስበር ወደ መጣበት በመመለስ አገሩን መታደጉን ተናግረዋል።

''የክልላችንም ሆነ የአገራችን ሰላም በዘላቂነት ማስጠበቅ የምንችለው ሁላችንም የቀደመውን የአብሮነት እሴት በማጎልበትና ማጠናከር ስንችል ነው'' ብለዋል።

ከስህተቱ የማይማረው አሸባሪው ህወሓት ዳግም ወረራ ለመፈጸም እየተዘጋጀ በመሆኑ ሕዝቡ በተደራጀ አግባብ አካባቢውን እንዲጠብቅ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።

የደብረ ታቦርና አካበባቢው ሕዝበ በተባበረ ክንድ የአሸባሪው ቡድን አገር የመበተን ህልምን መና እንዳስቀረው ሁሉ፤ ድሉን በልማት በመድገም  ድህነትን ታሪክ ለማድረግ መትጋት እንዳለበት አሳስበዋል።

የክልሉ መንግሥት በደብረ ታቦር ከተማ የሚከበረው የቅዱስ መርቆርዮስ በዓልና የፈረስ ጉግስ ውድድር  እንዲጎለብትና የቱሪስት መስህብ ለማድረግ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በአልና ውድድሩን ከአካባቢው ታሪክ ጋር በማስተሳሰር ገቢ እንዲያመነጭ ለማድረግ  ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ይርጋ ሲሳይ በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻችን ለማጥፋት አልሞ ያደረገው እንቅስቃሴ በተደራጀ የሕዝብ  ትግል መክሸፉን ተናግረዋል።

“ጠላትን የምናሸንፈውና ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻችንን የምናስቀጥለው ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አንድነታችንን ማጠናከር ስንችል ነው” ብለዋል።

የነጻነት ተምሳሌት የሆነውን የበጌምድር የፈረስ ጉግስ ውድድርና የቅዱስ መርቆርዮስ በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣የሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) እንዲመዘገብ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

''ለአገራችንና ለቤተ ክርስቲያናችን በአንድነት ልንቆም ይገባል'' ያሉት ደግሞ የደቡብ ጎንደር ዞን አገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ስዩማን ቀሲስ ምህረት ሞላ ናቸው።

"የበዓሉ ማድመቂያ የሆነው የፈረስ ጉግስ ውድድር በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅና የቱሪስት መስህብ ማድረግ ይገባል" ብለዋል ።

በበዓሉ ላይ የፌዴራል፣ የክልሉ፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ ታዋቂ አርቲስቶችና  የአካባቢው ማህበረሰብ ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም