ባለሥልጣኑ ለቢሮው ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የቢሮ ቁሳቁስና የተሽከርካሪ ድጋፍ አደረገ

69

ሚዛን፣ ጥር 25/2014/ (ኢዜአ) የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የቢሮ ቁሳቁስና ተሽከርካሪ ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን ዛሬ ቦንጋ ከተማ በመገኘት ያስረከቡት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታሁን ጋረደው ናቸው።

ዶክተር ጌታሁን በሥነስርዓቱ ላይ እንዳሉት ድጋፍ የተደረገው ክልሉ በቅርብ የተደራጀ እንደመሆኑ መጠን ሊያጋጥሙ የሚችሉ የአገልግሎት መስጫ ቁሳቁስ እጥረት ለማቃለል ታሳቢ በማድረግ ነው ።

ባለስልጣኑ የክልሉ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ የሚጠበቅበትን ተግባራት በአግባቡ ለመፈጸም የሚያግዙ አንድ ተሽከርካሪና  የቢሮ ቁሳቁስ  ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

በቀጣይም ለቢሮው ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠናና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ተልዕኮውን  እንዲያሳካ ባለስልጣኑ  የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል  ጠቁመዋል።

በተለይ ሁሉን አቀፍ የአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ተግባራት ለግብርና ልማት መሰረት በመሆኑ ቢሮው በዘርፉ ላይ  ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚጠበቅበትም አስገንዝበዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸው የአካባቢ ጥበቃና የደን ልማት ስራዎችን በሣይንሳዊ ዕውቀት ላይ ተመስርቶ ለመምራት ቢሮው አስፈላጊ ቁሳቁሶች ሊደራጅ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በባለስልጣኑ የተደረገው ድጋፍ ለስራው መሳለጥ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠሩም ባሻገር የክልሉን እምቅ የተፈጥሮ ፀጋ በአግባቡ በመንከባከብና በመጠበቅ ወደ ሀብት ለመቀየር የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ  ነው ብለዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የክልሉ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አሥራት ገብረማርያም የተደረገው ድጋፍ ቢሮው ያለበትን  የቁሳቁስ ችግር እንደሚያቃልል ተናግረዋል ።

በባለሥልጣኑ ከተደረገው ድጋፍ መካከል አንድ ሎንግ ቤዝ ቶዮታ ተሽከርካሪ፣ ለቢሮና አዳራሽ የሚሆኑ ዘመናዊ ወንበሮችና ጠረጴዛዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም  ላፕቶፕና ዴስክ ቶፕ ኮምፒዩተሮች፣ ለቢሮው ሥራ የሚያገለግሉ ካሜራዎች፣ ስካነሮች፣ ፕሪንተሮች  መሆናቸውን አስረድተዋል።

ቢሮው ሀብን ዘላቂነት መጠቀም እንዲቻል አካባቢን  የሚበክሉ ተግባራትን ለመከታተል፣ ለመቆጣጠር ጥፋት ተፈፅሞ ሲገኝ የእርምት እርምጃዎችን ለመውሰድና በዘርፍ የዳሰሳ ጥናቶችን ለማካሄድ መቋቋሙን ገልጸዋል።

ተልዕኮው ለመወጣት ቢሮው አስፈላጊ በሆኑ ሎጂስቲክና የሰው ኃይል ሊደራጅ እንደሚገባው ጠቁመው ከዚህ አንጻር ባለሥልጣኑ ያደረገው ድጋፍ ወሳኝ በመሆኑ አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም