የህብረቱ ጉባኤ እንግዶችን በመልካም መስተንግዶ ተቀብለን በማስተናገድ ኢትዮጵያ ሰላም መሆኗን የምናሳይበት መልካም አጋጣሚ ነው

73

ጥር 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) የህብረቱ ጉባኤ እንግዶችን በመልካም መስተንግዶ ተቀብለን በማስተናገድ ኢትዮጵያ ሰላም መሆኗን በተግባር የምናሳይበት መልካም አጋጣሚ ነው ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች አገልግሎት፤ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ዝግጅት እና በድርቁ ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በሚመለከት ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት ሚኒስትር ዴኤታዋ ሰላማዊት ካሣ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በርካታ ውጣ ውረዶች ታልፈው በአዲስ አበባ ለመካሄድ መብቃቱን አስታውሰዋል።

የህብረቱ ስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ስብሰባ በዛሬው እለት መጀመሩን ገልጸው፤ የህብረቱ ጉባኤ እንግዶችን በመልካም መስተንግዶ ተቀብለን በማስተናገድ ኢትዮጵያ ሰላም መሆኗን በተግባር የምናስመሰክርበት መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል።

የአፍሪካ አገራት ወንድምና እህቶቻችን እንዲሁም መሪዎቻቸው በፈተናችን ወቅት አብረውን ስለቆሙም እናመሰግናቸዋለን ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የአፍሪካን መሪዎች ተቀብላ ለማስተናገድ መቻሏ በራሱ ያለው ዲፐሎማሲያዊ ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ጉባኤው ያለምንም ችግር ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ በጸጥታና ደህንነት ግብረ ሃይሉ ልዩ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

ጉባኤው የኮቪድ-19 መከላከያ ፕሮቶኮልን ጠብቆ እንዲካሄድ ኢትዮጵያ የገባችውን ቃል ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆኗን ጠቁመዋል።

የድርቅ አደጋ በተከሰተባቸው የኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች በእንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን በመገንዘብ በሰዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሶማሌ ክልል በ9 ዞኖች በተከሰተው የድርቅ አደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ከ960 ሺህ በላይ ዜጎችን በማዕከል በማስገባት የዕለት ደራሽ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነም አንስተዋል።

እስከ ባለፈው ታህሳስ ወር ድረስ 558 ሺህ ኩንታል የምግብ እህል በማሰራጨት 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፤ በክልሉ በአጠቃላይ 3 ነጥብ 3 ሚሊየን ዜጎች የእለት ደራሽ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞንና በምስራቅ ባሌ በድርቁ ሳቢያ አደጋ ላጋጠማቸው ዜጎችም የዕለት ደራሽ ድጋፍ እየቀረበ መሆኑን አንስተው፤ በዞኑ ከ166 ሺህ በላይ ወገኖች በድርቁ ተጎጂ መሆናቸው ተለይቶ ወደ ዕለት ደራሽ ድጋፍ ማዕቀፍ እንዲገቡ መደረጉን ጠቅሰዋል።

በምስራቅ ባሌ በድርቁ ጉዳት የደረሰባቸውን ከ251 ሺህ በላይ ዜጎች በመለየት 42 ሺህ ኩንታል የዕለት ደራሽ ድጋፍ መሰጠቱን ተናግረዋል።

በደቡብ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን በድርቅ ሳቢያ ተጎጂ ለሆኑ ከ77 ሺህ በላይ ዜጎች ከ11 ሺህ ኩንታል በላይ የእለት ደራሽ ምግብ ድጋፍ መሰራጨቱ ተገልጿል።

በድርቅ ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለመደገፍ መንግስት እያደረገ ካለው ጥረት በተጨማሪም ሁሉም የበኩሉን አስተጽኦ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል።

በትግራይ ክልልም ከዓለም አቀፉ የምግብ ፕሮግራምና ከሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ከሐምሌ ወር ጀምሮ እስካሁን 41 የአውሮፕላን በረራዎች በማድረግ ሰብዓዊ ድጋፍ መድረሱን ጠቁመዋል።

አሸባሪው ህወሓት በአፋር ክልል የዓብዓላ መተላለፊያ መንገድን የጦር አውድማ በማድረግ እርዳታ የጫኑ ከባድ መኪኖች ወደ ትግራይ እንዳይገቡ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም