በጦርነቱ ወቅት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የመደገፍና ተቋማትን መልሶ የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል

133

ጥር 25/2014 (ኢዜአ) በጦርነቱ ወቅት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የመደገፍና ተቋማትን መልሶ የመገንባት ስራ የጋራ ሃላፊነት በመሆኑ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማለዳ ፎምና ፕላስቲክ ፋብሪካ አስታወቀ።

ፋብሪካው በአሸባሪው ህወሃት ዘረፋና ወድመት ለተፈፀመበት የአጣዬ ሆስፒታል እና ለተፈናቀሉ ወገኖች 1 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

ፋብሪካው ድጋፉን ያደረገው በአሸባሪው ሸኔ ከምዕራብ ኦሮሚያ ተፈናቅለው ደብረ ብርሃን ከተማ ለሚገኙ ወገኖችና ለአጣዬ ሆስፒታል ነው።

ከፋብሪካው በአርቲስት ታምሩ ብርሃኑ አስተባባሪነት በተደረገው ድጋፍ በድምሩ 1 ሚሊዮን ብር የሚገመት ልዩ ልዩ ቁሳቁስ መሆኑ ታውቋል።

ለተፈናቀሉት ወገኖች የተደረገው ድጋፍ የዱቄት እና ሌሎች የምግብ ቁሳቁሶች ሲሆን ለአጣዬ ሆስፒታል ደግሞ ለአገልግሎት የሚረዱ ቁሳቁሶችን ነው።

የፋብሪካው ብራንድ ማኔጀር አቶ መሳይ አሰፋ፤ በጦርነቱ ወቅት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የመደገፍና ተቋማትን መልሶ የመገንባት ስራ የጋራ ሃላፊነት በመሆኑ ድጋፉን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

ፋብሪካው ከዚህ በፊትም ለደሴ ሪፈራል ሆስፒታል የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው ሌሎች ድርጅቶችም የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው ነው ያሉት።

በአሸባሪው የሸኔ ቡድን ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ከተማ በጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ዜጎች ለተደረገላቸው ድጋፍ አመሰግነዋል።

ከምዕራብ ሸዋ ደኖ እና ኖኖ ወረዳዎች ተፈናቅለው መምጣታቸውን ገልጸው መንግሥት የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር በመፍታት በዘላቂነት ወደ ቀያቸው እንዲመልሳቸው ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም