ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከናሚቢያና ካሜሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ተወያዩ

421

ጥር 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከናሚቢያና ካሜሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ውይይቱን ያደረጎት ከ40ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ጉባኤ ጎን ለጎን ነው፡፡

በዚህም ከናሚቢያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኔቱምቦ ናንዲ-እንዳይትዋ ጋር በሁለትዮሽና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ  በውይይታቸው ሁለቱም አገራት ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እንደሚሹ መናገራቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

የናሚቢያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሚቢያ ችግር በገጠማት ጊዜ ሁሉ  ኢትዮጵያ ሁሌም ከጎኗ መሆኗን መግለጻቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

በዚህም ናምቢያ በአህጉራዊም ሆነ ዓለም አቀፍ መድረኮች ከኢትዮጵያ ጎን እንደምትቆም ማረጋገጣቸውንም እንዲሁ፡፡

ናምቢያ ከኢትዮጵያ ጋር በመከላከያና ደህንነት፣ በአቪየሽን እና ቤቶች ልማት መስኮች በጋራ የመስራት ፍላጎት እንዳላት መግለጻቸውንም አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል፡፡

የናሚቢያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኔቱምቦ ናንዲ-እንዳይትዋ የኢትዮጵያ አቻቸው አቶ ደመቀ መኮንን በናሚቢያ ይፋዊ ጉብኝት እንዲያደርጉ ግብዣ ማቅረባቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው ናሚቢያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም አጋርነቷን በተግባር ማሳየቷን አንስተዋል ነው ያሉት አምባሳደር ዲና፡፡

ለአብነትም የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ኢትዮጵያን በሚመለከት ጠርቶት በነበረው ያልተገባ ስብሰባ ላይ ናሚቢያ ከኢትዮጵያ ጎን መቆሟን በማስታወስ ምስጋና ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከናሚቢያ ጋር ያላትን የሁለትዮሸና ባለብዙ ወገን አጋርነት ይበልጥ ማጠናከር እንደምትሻ መግለጻቸውንም አምባሳደር ዲና ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከካሜሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሌጄኡን ምቤላ ምቤላ ጋር የሁለቱ አገራት የሁለትዮሸ ግንኙነት በሚጠናከርበት ጉዳይ መክረዋል፡፡

የካሜሩኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሁለቱን አገራት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል የፖለቲካ ምክክር መድረክ እንዲዘጋጅ መጠየቃቸውን አምባሳደር ዲና ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

ካሜሩን በተለይ በግብርና፣ ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ዲፕሎማሲ መስክ ከኢትዮጵያ ጋር መስራት እንደምትሻ መግለጻቸውንም እንዲሁ፡፡

ኢትዮጵያ በካሜሩን ኤምባሲዋን እንድትከፍት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መጠየቃቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከካሜሩን ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደምትሰራ መናገራቸውንም አምባሳደር ዲና አራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼